Friday, December 14, 2012


የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገበያ አድማሱን ለማስፋት የሚያስችለውን ተግባራት አጠናክሮ በማከናውን ላይ ነው

  •  PDF
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የገበያ አድማሱን በማስፋት ለመንገደኞች ቀልጣፋና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ተግባራት አጠናክሮ በማከናውን ላይ እንደሚገኝ አስታወቀ።  አየር መንገዱ የዓለም የአየር መንገዶች ጥምረት በአባልነት የተቀላቀለበትን አንደኛ ዓመት ትናንት አክብሯል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አልያንስስና ስራቴጂክ ፕላን ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ይስሐቅ ዘወልዲ በተለይ እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ የዓለም የአየር መንገዶች ጥምረትን በአባልነት ከተቀላቀለ ጀምሮ ያለውን የገበያ ድርሻ ለማስፋት እየሰራ ነው።

ከአባል አየር መንገዶች ጋር ተከታታይ የበረራና የሽያጭ ፕሮግራሞችን በጋራ በማቀናጀት እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከራሱ የበረራ መዳረሻዎች በተጨማሪ የዓለም የአየር መንገዶች ጥምረት የበረራ መዳረሻዎችን በመጠቀም የገበያ አድማሱን ለማሳደግ አቅም ፈጥሮለታል ብለዋል።
አቶ ይስሐቅ እንዳሉት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከእያንዳንዱ የዓለም የአየር መንገዶች ጥምረት አባላት ጋር ያለውን የገበያ ግንኙነት በማጠናከር ላይ ነው።

አየር መንገዱ ከዓለም የአየር መንገዶች ጥምረት አባል ወኪሎች ጋር በትብብር ከመስራቱ በተጨማሪ በአፍሪካ የጥምረቱ አባል ከሆኑት የግብጽና የደቡብ አፍሪካ አየር መንገዶች ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓለም የአየር መንገዶች ጥምረት የ27 አገሮችን አየር መንገዶችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፤ በመጪው የአውሮፓውያን ዘመን የታይዋን አየር መንገድ በአባልነት ይቀላቀላል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኢዜአ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment