Friday, December 28, 2012


አርቲስቶችና የኪነጥበብ ባለሞያዎች በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ የተለያዩ ተቋማትን ጎበኙ

  •  PDF
አርቲስቶችና የኪነጥበብ ባለሞያዎች የሀገር መከላከያ የደረሰበትን የቴክኖሎጂ አቅም መገንዘባቸውን ገለፁ፡፡

በኢፌዴሪ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የተለያዩ ተቋማት ጉብኝት ያደረጉ አርቲስቶችና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተቋማቱ የደረሱበትን የቴክኖሎጂ ደረጃ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
በሙያቸውም የተቋማቱን የእድገት ደረጃዎች ወደ ህብረተሰቡ ለማድረስ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል፡፡

የመጀመሪያ ጉብኝታቸውን ታህሳስ 17/2005 ዓ.ም ያደረጉት በመከላከያ ኢንጅነሪንግ ኮሌጅ ነው፡፡ በ1989 የተመሰረተውና በ1992ዓ.ም የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ ተማሪዎቹን ያስመረቀው ኮሌጁ አሁን በ23 የትምህርት አይነቶች የመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በ10 የትምህርት አይነቶች ደግሞ በ2ተኛ ዲግሪ እያሰለጠነ ነው፡፡

የአርቲስቶቹና ኪነጥበብ ባለሙያዎች ሁለተኛው ጉብኝት ደግሞ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ነው፡
በአየር ሃይልም ከበረራ ስልጠና እስከ አየር ትርኢት ድረስ ባለሙያዎቹ ተመልክተዋል፡፡ አርቲስቶችም የአየር በረራ ተካፋይ ሆነዋል፡፡

በብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የደጀን አቪየሽን ኢንዱስትሪ እንዲሁም የቢሾፍቱ አውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪም የጉብኝቱ አካል ናቸው፡፡

የደጀን አቪየሽን ኢንዱስትሪ የተለያዩ ለውጊያና ለትራንስፖርት የሚውሉ ጄቶችና አውሮፕላኖችን ሙሉ ጥገና ያደርጋል፡፡ አነስተኛ መጠን ያላቸውን ሄሌኮፕተሮችም እያመረተ ነው፡፡ ለተለያዩ ጎረቤት አገሮች የጥገና አገልግሎትም ይሰጣል፡፡

የቢሾፍቱ አውቶሞቴቭ ኢንዱስትሪም የተለያዩ ቀላልና መካከለኛ ከባድ መኪኖችን ጨምሮ የኮንስትራክሽን መኪኖችን ይገጣጥማል፡፡

ይህንን ሁሉ የጎበኙት የኪነ ጥበብ ሰዎች ታዲያ ሀገራቸው የደረሰችበትን የቴክኖሎጂ አቅም መገንዛባቸውን ገልጸዋል፡፡

የቴክኖሎጂ እድገቱንም ለህብረተሰቡ ለማድረግ እንደሚሰሩም ቃል መግባታቸውን የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment