የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲአራት ድርጅቶችን ወደ ግል ሊያዛውር ነው
አዲስ አበባ፤ - የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ አራት ድርጅቶችን ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል ሊያዛውር መሆኑን አስታወቀ።በኤጀንሲው የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ወንዳአፍራሽ አሠፋ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ ወደ ግል የሚዛወሩት ጊዮን ሆቴል፣ አዶላ ወርቅ ማዕድን ኢንተርፕራይዝ፣ አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅትና የግብርና ሜካናይዜሽን ድርጅት ናቸው።
ድርጅቶቹ ወደ ግል የሚዛወሩት ከነሠራተኞቻቸው ሙሉ በሙሉ ይዘው መሆኑን ጠቁመው፤ ኤጀንሲው ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር አሁን ያወጣው ሁለተኛ ዙር ጨረታ ነው ብለዋል።
በመጀመሪያው ዙር ስድስት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር ጨረታ አውጥቶ እንደነበር አቶ ወንዳፍራሽ አስታውሰው፤ በመጀመሪያው ዙር ለጨረታ ከቀረቡት መካከል የኮንስትራክሽን ሥራዎችና ቡና ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ድርጅት፣ አዋሽ ወይን ጠጅ አክሲዮን ማህበርና ንግድ ማተሚያ ድርጅት ይገኙባቸዋል።
ሃማሬሳ የምግብ ዘይት አክሲዮን ማህበር፣ አርባ ጉጉ ቡና ተክልና ቢሊቶ ሲራሮ እርሻ የተቀሩት መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
ከእነዚህ ድርጅቶች ውስጥ 17 ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል እንዲዛወሩ ሲደረግ ሶስቱ ደግሞ በጋራ ልማት ነው የሚዛወሩት።
የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ በዘንድሮው በጀት ዓመት በአጠቃላይ 20 ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዛወር እንዳቀደ መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
No comments:
Post a Comment