From: ethiopianreporter.com
በአዳማ የተጀመረው የምርጫ ዋዜማ ውዝግብ መቋጫ አላገኘም
- ‹‹ምርጫ ቦርድ ከኢሕአዴግም በላይ ኢሕአዴግ ሆኗል›› ቅሬታ አቅራቢ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በመጪው ሚያዚያ ለሚካሄደው የአካባቢና የአዲስ አበባ አስተዳደር ምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ለማወያየት ከአንድ ወር በፊት ለሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አድርጎ በአዳማ ከተማ በተካሄደው ውይይት የተቀሰቀሰው ውዝግብ ቀጥሏል፡፡ ከምርጫው የጊዜ ሰሌዳ በፊት በወሳኝ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ መነጋገር እንፈልጋለን የማለት ጥያቄዎችን ያነሱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ያቀረቡት ቅሬታ ምላሽ አላገኘም፡፡
መድረክን ጨምሮ በተለይ 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሰባት አባላት ያሉት አንድ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመው 18 ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን ለምርጫ ቦርድና ለጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ ያቀረቡ ቢሆንም፣ ምርጫ ቦርድ አንዱንም ጥያቄ ሳይቀበል ሙሉ ለሙሉ ውድቅ አድርጓል፡፡
ኮሚቴው ያቀረባቸው ቅሬታዎች 18 ዋና ዋና ነጥቦችን አካቶ ቢይዝም፣ ምርጫ ቦርድ ግን አንዳቸውም በተገቢ መረጃና ማስረጃ አልተደገፉም በሚል ጥያቄውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ ኮሚቴው ካቀረባቸው ጥያቄዎች መካከል ገለልተኛ የሆኑ የምርጫ አስፈጻሚ አካላት እንዲመረጡ፣ በተቃዋሚዎች አባላትና ደጋፊዎች ላይ የሚደርሰው ወከባና ጫና እንዲቆም፣ በገዥው ፓርቲና በመንግሥት መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት እንዲኖር፣ ገዢው ፓርቲ የመንግሥትን ሀብት አላግባብ መጠቀም እንዲያቆም፣ አንድ ለአምስት በሚል በመላ አገሪቱ የተዘረጋው አወቃቀር ለድምፅ መግዣ ጥቅም እያዋለ መሆኑን፣ በሽብርተኝነት ሽፋን በእስር የዋሉት ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎች እንዲፈቱ፣ እንዲሁም ደግሞ ምርጫው ለገለልተኛ ታዛቢዎች ክፍት እንዲሆን የሚሉትና የመሳሰሉት ይገኙባቸዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነጋ ዱፊሳ ባለፈው ረቡዕ ቦርዱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እያንዳንዱን ቅሬታ በማንሳት አንድም ማስረጃ አልቀረበባቸውም በማለት ቦርዱ ቅሬታውን ሙሉ ለሙሉ ውድቅ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
ቦርዱ ይህንን መግለጫ በሰጠ ማግስት ጋዜጠኞችን ጠርቶ መግለጫ የሰጠው የ33 የፖለቲካ ፓርቲዎች ጊዜያዊ ኮሚቴ፣ በቦርዱ በተሰጠው መግለጫ እጅግ መደንገጡን በመግለጽ የአገሪቱን የዲሞክራሲ ሥርዓት ወደለየለት አምባገነንነት የሚመራ አካሄድ ብሎታል፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አስራት ጣሴ የቦርዱን መግለጫ ‹‹አሳፋሪ ነው፤›› ያሉ ሲሆን፣ ቢያንስ አንድ ወይም ሁለት ጥያቄዎች ባለመቀበሉ ‹‹ቦርዱ ከኢሕአዴግም በላይ ኢሕአዴግ ሆኗል፤›› ብለዋል፡፡ ሌሎችም የኮሚቴው አባላት እንዳስረዱት፣ የቀረቡት ጥያቄዎች በ33 የፖለቲካ ፓርቲዎች አይደለም በአንድ ፓርቲ ቢቀርቡ እንኳ ትኩረት ሊነፈጋቸው አይገባም፡፡
የኮሚቴው ዋና ጸሐፊ አቶ ግርማ በቀለ የምርጫ ቦርድ የኢሕአዴግ አገልጋይ ነው ብለው ‹‹ፈጣሪዬን አምናለሁ፣ ያመንኩትን አመልካለሁ፣ ያመለኩትን አገለግላለሁ፤›› በማለት ጋዜጠኞችን ፈገግ አስደርገዋል፡፡
የምርጫ ቦርድ ገለልተኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሰበት መምጣቱን የተናገሩት የኮሚቴው አባላት፣ ተቃዋሚዎች ለአካባቢ ምርጫ ትኩረት ሰጥተው መሳተፍ የሚፈልጉ ቢሆንም፣ ሆን ተብሎ ከተሳትፎ ውጪ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡ ያቀረቡዋቸው ቅሬታዎች የመድረክ አጀንዳ ናቸው በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ሁሉም የኮሚቴው አባላት፣ ይህ አባባል የኢሕአዴግ ፈጠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ካገኙት ደግሞ መድረክን ተቀላቅለው በጋራ መሥራት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
No comments:
Post a Comment