Wednesday, December 26, 2012


from:ethiopianreporter.com 

የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ስድስት ተከሳሾች ተከላከሉ ተባሉ


የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም ሙስና ፈጽመዋል በሚል በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል፣ ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ይዞ በመገኘት የሙስና ወንጀልና ትክክለኛ ያልሆነ የምዝገባ መረጃ የመስጠት ወንጀል ክስ የመሠረተባቸውን፣ በሰነድና በምስክሮች በማስረዳቱ የቀድሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ስድስት ተጠርጣሪዎች እንዲከላከሉ ከትናንት በስቲያ ብይን ተላለፈባቸው፡፡
ብይኑን ያስተላለፈው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ የወንጀል ችሎት ነው፡፡ ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው፣ የተመሰከረባቸውና እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው የቀድሞው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ የክልሉ አፈ ጉባዔ አቶ ሀብታሙ ሂካ፣ አቶ ጌዲዮን ደመቀ፣ አቶ አሰፋ ገበየሁ፣ አቶ ገዛኸኝ አድገህ፣ አቶ መክብብ ሞገስና የአቶ ሀብታሙ ወንድም አቶ ኃይለ ገብርኤል ሂካ ናቸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ክስ የተመሠረተባቸው ከፌዴራል መንግሥት በተገኘ ድጎማና በክልሉ በጀት ሊሠሩ የነበሩ ሦስት ፕሮጀክቶች ማለትም የጣና በለስ ሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት፣ የግልገል በለስ መምህራን ኮሌጅና አሶሳ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ግንባታ ጋር በተያያዘ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ከፌዴራል መንግሥት የተሰጠውን የድጎማ በጀት በመጠቀም፣ የዲዛይን ማማከርና የግንባታ ጨረታ በማውጣትና በማወዳደር በሕጋዊ መንገድን ማሠራት ሲገባቸው፣ በሕገወጥ መንገድ በስውር በመመሳጠርና ሕገወጥ የሆነ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር፣ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት መንቀሳቀሳቸውን የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል፡፡

በዚሁም መሠረት በመንግሥት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ አቶ ያረጋል አይሸሹም የክልሉ ፕሬዚዳንት ስለነበሩ ሕጋዊ መንገድ የተከተለ ጨረታ እንዲወጣ ከማድረግ ይልቅ፣ በወቅቱ የክልሉ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ከነበሩት አቶ ሀብታሙ ሂካ ጋር በመመካከርና የጨረታ ሰነድ እንዲያቀርቡላቸው በማድረግ ለካቢኔ አቅርበው ማስወሰናቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

በዚህ መሠረት የጨረታ ሰነዱን ካስወሰኑ በኋላ፣ አመለወርቅ ሳዲቅ የተባሉ ግለሰብን ኮንትራክተር እንዲያገናኙዋቸው ማድረጋቸውን ግለሰቧ ለዓቃቤ ሕግ ምስክር ሆነው በሰጡት ቃል መስክረዋል፡፡ ግለሰቧም ጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት ባለቤትን አቶ ጌዲዮንን ማገናኘታቸውን ምስክሯ ተናግረዋል፡፡

ዲዛይኑንና የማማከሩን ሥራ የአቶ ጌዲዮን ድርጅት እንዲያሸንፍና የግንባታውን ጨረታ እሱ እንዲያጫርት በማድረግ፣ የአቶ ገዛኸኝ አድገህ ድርጅት “ጋድ ኮንስትራክሽን” እንዲያሸንፍ ያደርጋሉ፡፡ ጋድ ኮንስትራክሽን የግልገል በለስ መምህራን ኮሌጅንና የጣና በለስ የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤትን እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡

የአሶሳን ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋምን የማማከርና የዲዛይን ሥራ ጨረታ በድጋሚ ጌዲዮን ደመቀ የዲዛይንና ማማከር ድርጅት ማሸነፉን ክሱ ያስረዳል፡፡

ጌዲዮን ደመቀ አማካሪ በድጋሚ የኮሌጁን ግንባታ ጨረታ አጫርቶ የአቶ መክብብ ሞገስ ድርጅት ኮለን ኮንስትራክሽን የተባለ ድርጅት እንዲያሸንፍ ይደረጋል፡፡ ፕሬዚዳንቱና የትምህርት ቢሮ ኃላፊው ከድርጅቶቹ 250 ሺሕ ብር እንዲከፈላቸው መስማማታቸውንና የክልሉ ትምህርት ቢሮ መሐንዲስም እንዲካፈሉ መደረጉን ምስክሮቹ ማለትም መሐንዲሱና ወይዘሮ አመለወርቅ ሳዲቅ የተባሉት የዓቃቤ ሕግ ምስክር አረጋግጠዋል፡፡ አቶ ያረጋል አይሸሹምና አቶ ሀብታሙ ሂካ ከጌዲዮን ደመቀ አማካሪ ድርጅት 50 ሺሕ ብርና በየወሩ አሥር ሺሕ ብር እንዲከፈላቸው መስማማታቸውን ምስክሮቹ አስረድተዋል፡፡ አቶ ጌዲዮን ደመቀ የኮንስትራክሽን ጨረታውን እንዲያጫርቱ የትምህርት ቢሮ ኃላፊው አቶ ሀብታሙ ውክልና መስጠታቸውም ተጠቅሷል፡፡
አቶ ጌዲዮን ደመቀ የአሶሳን ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ግንባታ የአቶ መክብብ ድርጅቶች እንዲያሸንፉ ሲያደርጉ፣ ለአቶ ያረጋልና ለአቶ ሀብታሙ አሸናፊው ድርጅት 700 ሺሕ ብር ሊከፍል መስማማቱን ምስክሯ ተናግረዋል፡፡

ለምስክሯ ደግሞ 150 ሺሕ ብር ሊሰጣቸው ተስማምቶ እንደነበርም ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ያረጋል በራሳቸው፣ በባለቤታቸው ወይዘሮ ትዕግስት ቸኮልና በሕፃናት ልጆቻቸው ስም ተመዝግበው የተገኙ ሕንፃዎችና ኮንዶሚኒየም ቤቶች መኖራቸውን፣ በባንክ ገንዘብ መገኘቱንና በሀብት ማስመዝገብ አዋጁ መሠረት ሀብታቸውን አለማስመዝገባቸውንና ተደብቆ የተገኘ ምንጩ ያልታወቀ ሀብት መገኘቱ በክሱ ተዘርዝሯል፡፡

አቶ ሀብታሙ ሂካም መጨረሻ ላይ ማለትም እጃቸው ሲያዝ የክልሉ አፈ ጉባዔ እንደነበሩና ይከፈላቸው የነበረው ደመወዝ ከስድስት ሺሕ በላይ ቢሆንም ይዘውት የተገኘው ሀብት ያለአግባብ የተገኘ መሆኑን፣ ወንድማቸው አቶ ኃይለ ገብርኤል ሂካ ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁት በ1996 ዓ.ም. ሐምሌ ወር መሆኑ ቢታወቅም፣ በስማቸው እያንዳንዳቸው 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያሏቸው ሁለት ድርጅቶች እንዳሏቸውና ምንጩ ያልታወቀ ንብረት ይዘው መገኘታቸውን ክሱ ያብራራል፡፡

ዓቃቤ ሕግ ሰባት የሰው ምስክሮችን ያቀረበ ሲሆን፣ በዋነኛነት የክልሉ የትምህርት ቢሮ መሐንዲስ፣ አዲስ አበባ የሚኖሩትና በዋናነት ወንጀሉን ያጋለጡት ወይዘሮ አመለወርቅ ሳዲቅ የተባሉ ግለሰብና አቶ አነዚር ኢብራሂም ኤንዘር የክልሉ የካቢኔ አባልና የአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊ እንደክሱ በማስረዳታቸው፣ ተጠርጣሪዎቹ እንዲከላከሉ ፍርድ ቤቱ ብይን አስተላልፏል፡፡ ተጠርጣሪዎቹ የመከላከያ ምስክሮቻቸውን አቅርበው እንዲያስረዱ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment