Friday, December 28, 2012


በቲቢ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ተገለፀ

  •  PDF
በኢትዮጵያ በቲቢ በሽታ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታወቀ።

በፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የቲቢ መከላከያና ቁጥጥር ፕሮግራም ቴክኒካል አማካሪ ዶክተር አንዳርጋቸው ቁምሳ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በ1990ዎቹ በቲቢ በሽታ ከሚያዙ 100 ሺ ሰዎች መካከል በአመት 500 ይሞቱ የነበረውን በአሁኑ ወቅት ወደ 240 ዝቅ ማድረግ ተችሏል።

ታማሚዎች ተገቢውን ህክምና በወቅቱ እንዲያገኙ በመደረጉና ህክምናቸውን እንዲከታተሉ በመደረጉ በሽታው ሊቀንስ መቻሉን ዶክተር አንዳርጋቸው ገልፀው፤ በተለይም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመቱ መጨረሻ አሁን የተገኘውን ቁጥር ይበልጥ በመቀነስ ወደ 156 ዝቅ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው የበጀት ዓመትም የቲቢ በሽታ ህክምና ካደረጉ 159 ሺ ሰዎች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ሙሉ በሙሉ የህክምና ክትትል በማግኘታቸው ከበሽታቸው መዳን መቻላቸውን ገልፀዋል።

ቀደም ሲል የቲቢ በሽታ ምርመራና የህክምና አገልግሎት መስጫዎች ጣቢያዎች ውስንነት እንደነበር ያስታወሱት ዶክተር አንዳርጋቸው፤ በአሁኑ ወቅት በመላ ሃገሪቱ በሚገኙት ከ3ሺ በላይ የጤና ጣቢያዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡና የጤና ባለሙያዎች በቲቢ በሽታ ላይ ያላቸውን ክህሎት እንዲያሻሽሉ ለማስቻል የተለያዩ ስልጠናዎች መሰጠቱን ጠቁመው፤ በተያዘው የበጀት ዓመትም መድሀኒት በተላመዱ የቲቢ በሽታዎች ላይ ከሁሉም ክልሎች ለተውጣጡ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።

እንዲሁም የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኞች አቅምን በማሳደግ በሽታውን ይበልጥ ለመከላከል  ስልጠና ለመስጠት በእቅድ መያዙን ተናግረዋል።

የቲቢ በሽታ ሥርጭትን በይበልጥ ለመከላከል ጥረት ማድረግ  እንደሚያስፈልግ  የገለጹት ዶክተር አንዳርጋቸው፤ በሽታውን ለመከላከል ማንኛውም ዜጋ የበሽታውን ምልክት  በሚያይበት ወቅት ወደ ህክምና ተቋማት  መሄድ መከላከል እንደሚገባው አሳስበዋል።

No comments:

Post a Comment