ኔልሰን ማንዴላ ከሆስፒታል ወጡ
ታዋቂው የነጻነት ታጋይና የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ ከሆስፒታል ወጡ። ኢዜአ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ጠቅሶ አንደዘገበው ማንዴላ ከሕክምና የወጡት ለ18 ቀናት ሲከታተሉ ከቆዩ በኋላ ነው። ከፕሬዚዳንት ጃኮቭ ዙማ ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንደሚያመለክተው ማንዴላ በጆሃንስበርግ መኖሪያ ቤታቸው ሕክምናቸውን ይከታተላሉ። የዘጠና አራት ዓመቱ አዛውንት በሳንባና በጣፊያ በሽታዎች ተይዘው ሕክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተዋል። ባለቤታቸው ግራሳ ማሼል ማንዴላ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙና መንፈሳቸው መልካም መሆኑን ተናግረዋል። ፕሬዚዳንት ዙማ ደቡብ አፍሪካያውያን ለሏኩላቸው የገና በዓል መልካም ምኞት መግለጫዎች አመስግነዋል። የልጅ ልጃቸው ማንድላ ገናን ካለ እሳቸው በማክበራችን በእጅጉ አዝነው እንደነበር ገልጸው፣''ለዚያን ያህል ጊዜ ከአጠገባችን ይለያሉ ብለን አላሰብንም ነበር?'' ሲሉ ተናግረዋል። ማንዴላ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1990 ከሆስፒታል ከወጡ በኋላ እንደ አሁኑ ለረጅም ጊዜ በሆስፒታል ቆይተው እንደማያውቁ ዘገባዎቹ አስታውሰዋል። ባለፉት ሁለት ዓመታት ለሦስት ጊዜ ሆስፒታል ገብተው ነበር። ማንዴላ በደቡብ አፍሪካ ሰፍኖ የኖረውን የዘር መድልኦ ሥርዓት(አፓርታይድ) በመታገላቸው ለ27 ዓመታት በሮቢን ደሴት ታስረው እንደነበር ይታወቃል። ታዋቂው ታጋይ አገራቸውን ለአምስት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት መምራታቸውንም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዘገባው አስታውቋል። |
No comments:
Post a Comment