Monday, December 31, 2012


from: ethiopianreporter.com

ፓርላማው የአቶ ጁነዲን ሳዶን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ነው

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) በቅርቡ ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትርነታቸው የተነሱትን የአቶ ጁነዲን ሳዶ ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ መሆኑን ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለጹ፡፡
ፓርላማው የአቶ ጁነዲን ሳዶን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ነው
የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ምንጮች ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አቶ ጁነዲን በፓርላማ የሥነ ሥርዓት ደንብ መሠረት ሊጠየቁበት የሚችል የሕግ ጉዳይ ሊኖር ስለሚችል፣ በምክር ቤት አባልነታቸው ያገኙትን ያለመከሰስ መብት ምክር ቤቱ እንዲያነሳ የሚጠይቅ ደብዳቤ በመንግሥት ቀርቧል፡፡ ጥያቄው በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኩማ ደመቅሳ ወይም በፍትሕ ሚኒስትሩ አቶ ብርሃን ኃይሉ በኩል መቅረብ ያለበት መሆኑን የምክር ቤቱ ደንብ ያዛል የሚሉት እነዚሁ ምንጮች፣ ጥያቄው በየትኛው አካል መቅረቡን ለመረዳት እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡

ባለፈው ሐሙስ የዓመቱን ዘጠነኛ ስብሰባውን ያካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአምስት አጀንዳዎች ላይ ለመወያየት ፕሮግራም ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በአራቱ ላይ ብቻ ተወያይቶ የቀረውን ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፎታል፡፡

የስምንተኛ መደበኛ ስብሰባውን ቃለ ጉባዔ፣ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረትን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብንና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመቆጣጠር የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፣ እንዲሁም ሁለት የተለያዩ ዓለም አቀፍ የብድርና የትብብር ስምምነቶችን ማፅደቅ በዕለቱ የተወያየባቸውና ውሳኔ ያሳለፈባቸው አጀንዳዎች ናቸው፡፡ በአምስተኛ አጀንዳነት ተይዞ የነበረው “የአንድ የምክር ቤት አባልን የሕግ ከለላ ስለማንሳት የቀረበ የውሳኔ ሐሳብን መርምሮ ማፅደቅ” የሚል ቢሆንም፣ የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አባዱላ ገመዳ ይህንን አጀንዳ በቀጣይ ስብሰባ ለመመልከት ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፈውታል፡፡

የምክር ቤቱ አባላት ለጉባዔው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ቀደም ብለው በማወቅ በጉዳዩ ላይ የሚቀርቡ ሰነዶች ካሉ ደግሞ ሰነዶቹ ከውይይቱ ሦስት ቀናት በፊት እንዲደርሳቸው የምክር ቤቱ የአሠራር ደንብ ቢደነግግም፣ የሕግ ከለላን ስለማንሳት ቀርቦ ስለነበረው አጀንዳ የቀረበላቸው ምንም ዓይነት ሰነድ እንደሌለ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የሕግ ከለላው እንዲነሳ ጥያቄ የቀረበበት የምክር ቤት አባል ማንነት በይፋ ባይገለጽም፣ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ የአቶ ጁነዲን ሳዶ ጉዳይ መሆኑን እንደተረዱ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ ጁነዲን ሳዶ በአሁኑ ወቅት በሽብር ተግባር ተጠርጥረው በእስር ላይ ከሚገኙት ባለቤታቸው ወ/ሮ ሐቢባ መሐመድ ጋር በተያያዘ፣ በድርጅታቸው ኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ተገምግመው ከፓርቲው ከፍተኛ አመራርነት ወደ ተራ አባልነት ዝቅ መደረጋቸው ይታወሳል፡፡

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በፓርላማ በፀደቀላቸው የሚኒስትሮች ሹመት ደግሞ ከሲቪል ሚኒስትርነታቸው መነሳታቸውን ሪፖርተር ዘግቧል፡፡ 

No comments:

Post a Comment