Monday, December 31, 2012


from:ethiopianreporter.com

ለዓይነስውራን መፍትሔ የሰጡት ዓይነስውር

ፒያሳ በተለምዶ ኢትሆፍ ተብሎ ከሚጠራው ድርጅት ፊት ለፊት አገልግሎቱ ለየት ያለ የኢንተርኔት ካፌ ተክፍቷል፡፡ በካፌው ያለው የኢንተርኔት አገልግሎት ዓይነስውራን ያለማንም ዕርዳታ ግላዊ የሆኑ የአሌክትሮኒክስ መልዕክቶቻቸውን ኢ-ሜይል እንዲያዳምጡና ራሳቸው መልዕክታቸውን ጽፈው እንዲልኩ የሚያስችል ነው፡፡ ‹‹ኢትዮፒክ ብሬል›› የተሰኘን ፕሮግራም ‹‹ለዓይነስውራን አመቺ የዴስክቶፕ መጠቀሚያ›› (None visual desktop access NVDA) የተሰኘ ሶፍትዌር ውስጥ ተካትቶ ለኢትዮጵያውያን አገልግሎት መሰጠት ከጀመረ ሳምንት አልፎታል፡፡  

ዓይነስውራን በነፃ እንዲጠቀሙበት የተዘጋጀው ይህ ሶፍትዌር ‹‹ስክሪን ሪደር›› የሚባል ፕሮግራም ይዟል፡፡ በመሆኑም ሶፍትዌሩ ዓይነስውራኑ የሚጠቀሙበት ኮምፒውተር ላይ ሲገጠም ኮምፒውተሩ ላይ የሚገኙ መረጃዎችን በሙሉ በማዳመጥ መጠቀም ያስችላል፡፡ 

ሶፍትዌሩ ‹‹ኢትዮፒክ ብሬል›› የተሰኘው ፕሮግራም ስለተካተተበት ዓይነስውራን የመጣላቸውን መልዕክት ወደ ማንኛውም የአገር ውስጥ ቋንቋዎች ቀይሮ እንዲያዳምጡ ይረዳል፡፡ ሶፍትዌሩ ላይ የ‹‹ኢትዮፒክ ብሬል›› ፕሮግራምን ለማካተት ብሬል ዲስፕሌይ የተሰኘውን ፕሮግራም ተጠቅመው የሠሩት ነዋሪነታቸውን በካናዳ ያደረጉት ዓይነስውሩ ዶክተር ታምሩ እውነቱ ናቸው፡፡

ዶክተር ታምሩ ዶክትሬታቸውን በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሠርተዋል፡፡ የሳውንድ ኢንጂነሪንግ ባለሙያ ሲሆኑ የአዳፕቲቭ ቴክኖሎጂን በማማከር ሥራ ላይም ተሰማርተዋል፡፡ ‹‹ዓይነስውር የሆነ ግለሰብ  ኢንተርኔትን ብቻውን መጠቀም ያለመቻልን ችግር በራሴ ያየሁት በመሆኑ ሶፍተዌሩ ላይ የኢትዮፒክ ብሬል ፕሮግራም እንዲካተት ፕሮግራሙን ሠርቻለሁ፤›› ያሉት ዶክተር ታምሩ፣ ‹‹ተስማሚ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለዓይነስውራን›› የሚል መጠሪያ ያለውን የኢንተርኔት ካፌ ከፍተዋል፡፡

ሶፍትዌሩ ማንኛውም ሰው የሚጠቀምበት ኮምፒውተር ላይ መገጠም ይችላል፡፡ ባለው የድምፅ ሲስተም በመታገዝም ኮምፒውተሩ ስክሪን ላይ ያለውን ጽሑፍ ይናገራል፡፡ ኮምፒውተሩ ላይ ያሉት የመተየቢያ ቁልፎች ላይ ያሉት ፊደሎች ሲነኩ ሶፍትዌሩ ባለው የድምፅ ሲስተም የተጫኑትን ፊደል ያሰማል፡፡

ይህ ሶፍትዌር ማንኛውም ኮምፒውተር ላይ ያለምንም ገደብ እንዲገጠም ተደርጎ የተሠራ በመሆኑ፣ ግለሰቦች በሚዋሱት ላፕቶፕ አሊያም በሚሔዱበት ቦታዎች ላይ በሚያጋጥሟቸው ኮምፒውተሮች ላይ ሁሉ በቀላሉ እንዲጫን ተደርጎ ተሠርቷል፡፡ ሶፍትዌሩን ፍላሽዲስክ ላይ አሊያም ሲዲ ላይ መገልበጥ የሚቻል በመሆኑ ማንኛውም ኮምፒውተር ላይ ሲዲው ሲከተት ወይም ፍላሹ ሲሰካ ሶፍተዌሩ ራሱን አስነስቶ ለጥቅም ዝግጁ ይሆናል፡፡ በመሆኑም ሶፍዌሩ ኮምፒውተሮቻቸው ላይ እንዲገጠምባቸው የማይፈልጉ ሰዎች፣ ዓይነስውራን ሶፍተዌሩን በቀጥታ ከሲዲው ወይም ከፍላሽ ዲስኩ ላይ እንዲጠቀሙ ተደርጎ የተመቻቸም ነው፡፡ ይህ በመሆኑ ደግሞ ኢንተርኔት መጠቀም የሚፈልጉ ዓይነስውራን በወዳጅ ቤትም፣ በቤተ መጻሕፍትም ሆነ በኢንተርኔት ካፌ ሲጠቀሙ ‹‹አንዴ አንብቡልኝ›› ወይም ‹‹አንዴ ጻፉልኝ›› የሚለውን ጥገኝነት ያስቀራል፡፡ ለተጨማሪ ቀላል አጠቃቀምም ሶፍተዌሩ ወደሚሞሪ ካርድ እንዲገለበጥ እንደሚደረግም ዶክተር ታምሩ ተናግረዋል፡፡ 

ፕሮግራሙን ሠርቶ ለማጠናቀቅ አራት ዓመታትን የወሰደ ሲሆን አማርኛን ጨምሮ ከ50 በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ያስጠቅማል፡፡ 

ኢንተርኔት ካፌው አገልግሎት የሚሰጠው ለዓይነስውራን ብቻ ሳይሆን ማየት ለሚችሉም ግለሰቦች በመሆኑ፣ ዓይነ ስውራን ማየት ከሚችሉት ጋር በአንድ ላይ ኢንተርኔትን ለመጠቀም መገናኘታቸው ማኅበራዊ ግንኙነታቸውን ከማጠናከሩ ባሻገር የተለያዩ የቴክኖሎጂ ዕውቀቶችን እንዲለዋወጡ ምክንያት እንደሚሆን ዶክተሩ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ታምሩ የዛሬ 12 ዓመት ‹‹ተስማሚ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለአይነስውራን›› የሚል ድርጅት አቋቁመዋል፡፡ ‹‹ማየት ባልችልም ራዕይ አለኝ›› የሚል መሪ መልዕክት ያለው ይህ ድርጅት የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ሲኖረው ኮሌጁ ለዓይነስውራን የኮምፒውተር ሥልጠና ይሰጣል፡፡ በተጨማሪም ከዜሮ ክፍል እስከ ዩኒቨርስቲ ያሉ ተማሪዎች የሚማሩባቸውን የትምህርት መርጃ መጻሕፍት፣ ትምህርት በሚሰጥባቸው ቋንቋዎች ወደ ብሬል ይቀይራል፡፡ ይሁንና ከዚህ ቀደም በነበረው አሠራር መጻሕፍትን ወደ ብሬል የሚቀየረው በእንግሊዝኛና በአማርኛ ቋንቋዎች ብቻ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ላይ ግን ዓይነስውራን በሚማሩበትና በሚኖሩበት አካባቢ በሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ የትምህርት መጻሕፍትን ወደ ብሬል እንዲቀየር እንቅስቃሴ እያደረገ ነው፡፡ 

No comments:

Post a Comment