Tuesday, June 11, 2013

ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሚ እንደምትሆን ገለፀች

ሱዳን ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሚ እንደምትሆን ገለፀች 

የሱዳን ማስታወቂያ ሚኒስትርና የመንግስት ቃል አቀባይ አህመድ ቢላል ዑስማን ሀገራቸው ኢትዮጵያ እያስገነባችው ካለው ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሚ እንደምትሆን ገለፁ፡፡
ኢትዮጵያ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ላይ ሱዳን ተሳታፊ እንድትሆን ማድረግዋን ቃለ አቀባዩ አህመድ ቢላል ዑስማን ገልፀዋል፡፡ 
ግድቡ የሚያደርሰው ጉዳት ካለም ለማጣራት ከኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብፅ እንዲሁም ከአለምአቀፍ ባለሞያዎች የተወውጣጡ አስር አባላት ያለው ኮሚቴ ተቋቁሞ የማጣራት ስራውን በማከናወን ስጋቱ መልስ እንዲያገኝ  አድርጓል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ሱዳን ኢትዮጵያ ከምታስገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠቃሚ ስለምትሆን ለግድቡ ስኬት ባለሞያዎችና ቴክኒሻኖች ወደ ኢትዮጵያ ለመላክ ዝግጁ ነች ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ከግብፅ ባለስልጣናት ለመምከርም በሱዳን የውሃና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ኦሳማ ዓብደላ መሓመድ አል-ሓሰን የሚመራ ልኡክ በዚህ ሳምንት ወደ ግብፅ እንደሚያመራ ገልፀዋል፡፡
ግድቡ ተደርምሶ በሱዳን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተብሎ ለሚነሳ ስጋትም ደረጃውን በጠበቀ የዘመኑ ቴክኖሎጂ ተደግፎ እየተገነባ በመሆኑ ምንም አይነት ሰጋት እንደማይፈጥር ተናግረዋል፡፡

No comments:

Post a Comment