Tuesday, June 11, 2013

ሸራተን አዲስ ተከሰሰ 

“የተጣለበትን ግዴታ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ አይደለም” መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር 
“ተቀራርቦ በመወያየት መፍታት ሲቻል ለክርክር መድረክ ማቅረብ ያሳዝናል” ሸራተን አዲስ ሆቴል

ከአራት ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ. ማርች 1 ቀን 2011 ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የኅብረት ስምምነት ሲያደርጉ ሸራተን አዲስ ተግባራዊ ሊያደርጋቸው ከስምምነት ላይ የደረሰባቸውን ግዴታዎች ተግባራዊ ሊያደርግ አለመቻሉን በመጥቀስ፣ የሸራተን አዲስ ሆቴል መሠረታዊ የሠራተኞች ማኅበር ክስ መሠረተ፡፡
ለተመሠረተበት ክስ የመቃወሚያ ምላሽ የሰጠው ሸራተን አዲስ በበኩሉ፣ ችግሮች እንኳ ቢኖሩ ተቀራርቦ መፍትሔ ማግኘት ሲቻል ወደ ክርክር መድረክ ማቅረቡ ተገቢ አለመሆኑን ገልጿል፡፡ 
ሠራተኛ ማኅበሩ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ባቀረበው ክስ እንደገለጸው፣ ሁለቱ ወገኖች እ.ኤ.አ. ማርች 1 ቀን 2011 ለሦስት ዓመታት የሚቆይ የኅብረት ስምምነት ፈጽመዋል፡፡ ማኅበሩ ሊፈጽማቸው የሚገቡ ግዴታዎች አሉበት፡፡ ሆቴሉም በስምምነቱ መሠረት ሊፈጽማቸው የሚገቡ ግዴታዎች አሉ፡፡ ሆቴሉ የተወሰኑ ግዴታዎችን የፈጸመ ቢሆንም ያልፈጸማቸው ነገር ግን ለመፈጸም ግዴታ የገባባቸው ስምምነቶች ቢኖሩም ሊፈጽም ባለመቻሉ፣ ማኅበሩ በተደጋጋሚ በቃልና በጽሑፍ ቢያሳስብም፣ ከሆቴሉ ምላሽ ባለማግኘቱ ጉዳዩን ወደ ሕግ መውሰዱን የክስ ቻርጁ ያብራራል፡፡
ሆቴሉ ሊተገብራቸው ሲገባ ስምምነቱን ወደጐን በመተው እንደ ስምምነቱ አለመፈጸሙን በመግለጽ ማኅበሩ ለቦርዱ ባቀረበው ክስ ውስጥ የጠቀሳቸው 12 ግዴታዎች ናቸው፡፡ ማኅበሩ ለቦርዱ ባቀረበው ክስ ላይ እንዳብራራው፣ ሆቴሉ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ የተሰጠውን ኃላፊነት የሚያሳይ የሥራ ዝርዝር (Job Description) አልሰጠም፡፡ ደረጃውን የጠበቀ የአደጋ መከላከያ የመስጠት ግዴታ ቢኖርበትም፣ ባለመስጠቱ በሠራተኞች ላይ አደጋ ደርሷል፡፡ ሠራተኞች የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመውሰድ ችሎታቸውን እንዲያዳብሩ በዓመት 250 ሺሕ ብር ለመስጠት የተስማማ ቢሆንም ግዴታውን አለመወጣቱን፣ በሆቴሉ ውስጥ በሚፈጠር ጥፋት የጥፋተኝነት ምርመራ ሲደረግ የማኅበሩ ተወካይ እንዲኖር የተደረሰውን ስምምነት በመጣስ፣ ተወካይ እንዲኖር ፈቃደኛ አለመሆኑን ክሱ ይገልጻል፡፡
በሥራ ድርሻቸው ብልጫ ላሳዩ ሠራተኞች ሽልማት እንደሚዘጋጅ ይህም የማኅበሩ ተወካይ በዝግጅቱ ውስጥ እንዲኖር ቢስማማም፣ ለማኅበሩ ግልጽ ባልሆነ ሁኔታ በአንድ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ሠራተኞችን በመለየት ቦነስ መሰጠቱንና ተገቢ አለመሆኑን ማኅበሩ በክሱ ጠቅሷል፡፡
በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁጥር 377/96 አንቀጽ 61(1) መሠረት የአንድ ሠራተኛ መደበኛ የሥራ ሰዓት በቀን ስምንት ሰዓታት እንዲሁም በሳምንት ከ48 ሰዓታት መብለጥ እንደሌለበት መደንገጉን ያስታወሰው ማኅበሩ፣ የሆቴሉ ሠራተኞች በአንዱ ፈረቃና በሌላኛው ፈረቃ መካከል በቂ ዕረፍት በማያገኙበት ሁኔታ እንዲሠሩ ማድረጉን ተቃውሟል፡፡ ለሠራተኞች የተገዛን የመድን ዋስትና ፖሊሲ ለማኅበሩ መስጠት ሲገባው ሆቴሉ አለመስጠቱን፣ ነፍሰጡር የሆነች ሠራተኛ ከወሊድ በፊትና በወሊድ ጊዜ ከሚኖራት የቀዶ ሕክምና ውጪ ላሉ የሕክምና ወጪዎች ሆቴሉ እስከ ሦስት ሺሕ ብር ወጪ የሚሸፍን ቢሆንም፣ ከወጪው ላይ የገቢ ግብር እየቀነሰ መክፈሉ በአዋጁ አንቀጽ 29(8) መሠረት አግባብ አለመሆኑን አስረድቷል፡፡
የአገልግሎት ክፍያን በተመለከተ የወጪ ሒሳብ ተቆጣጣሪን ሪፖርት ለማኅበሩ በየዓመቱ ለመስጠት በኅብረት ስምምነቱ የተስማማ ቢሆንም ግዴታውን አለመወጣቱን፣ በሆቴሉ ክፍት የሥራ ቦታ ላይ ሠራተኞችን አወዳድሮ ለመቅጠር ሲፈለግ፣ ግልጽነት እንዲኖረው የውድድሩ ውጤት በማስታወቂያ ሰሌዳ ላይ እንዲለጠፍ የተደረሰውንም ስምምነት አለመቀበሉንና ተግባራዊ እያደረገው አለመሆኑን አክሏል፡፡
የሸራተን አዲስ መሠረታዊ ሠራተኞች ማኅበር በክሱ ሌላው ያካተተው ነጥብ፣ ሆቴሉ በሌሊት ፈረቃ ለሚሠሩ ሠራተኞች የቤታቸው መግቢያ ለትራንስፖርት አመቺ እስከሆነ ድረስ፣ ትራንስፖርት የማዘጋጀት ግዴታ ያለበት ቢሆንም፣ ተግባራዊ ባለማድረጉ አንዳንድ ሠራተኞች በጨለማ ወንጀል ፈጻሚዎች እንዲጋለጡ ማድረጉን ተናግሯል፡፡ ሠራተኛ ሲያገባ አምስት ቀናት የደስታ ፈቃድ እንዲሁም የዘመድ ሞት ሲያጋጥመው ሦስት ቀናት የሐዘን ፈቃድ እንደሚሰጠው በኅብረት ስምምነቱ የተካተተ ቢሆንም፣ በዕረፍት ላይ ያለን ሠራተኛ አያካትትም በማለት ስምምነቱን እየጣሰ መሆኑን በማብራራት፣ ቦርዱ ማኅበሩ ባቀረባቸው በሁሉም ጥያቄዎች ላይ እንደ ክሱ ዳኝነት እንዲሰጠው በክስ ቻርጁ አስፍሯል፡፡
ሆቴሉ በበኩሉ በሰጠው ምላሽ ክሱ መቅረብ ያለበት በመደበኛ የፌዴራል የሥራ ክርክር ፍርድ ቤት እንጂ፣ በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ አለመሆኑን በመጥቀስ ክሱን ተቃውሟል፡፡ በምክንያትነት ያቀረበውም ነባር መብቶችንና ጥቅሞችን ለማስከበር የሚቀርብ የዳኝነት ጥያቄ የግል የሥራ ክርክር መሆኑን አዋጅ ቁጥር 138ን በመጥቀስ ነው፡፡
ሠራተኛ ማኅበሩ ያቀረበው የክርክር ጭብጥ የጥቂት ሠራተኞችን መብቶችና ጥቅሞች በሚመለከት በመሆኑ፣ ክርክሩ የግል የሥራ ክርክር እንጂ የውል የሥራ ክርክር አለመሆኑን የጠቆመው ሆቴሉ፣ የግል የሥራ ክርክርን ቦርዱ ሊያይ እንደማይችልም አስታውቋል፡፡ ጉዳዩ በቅድሚያ በአስማሚ የመታየትን ሥርዓት ሳይካሄድበት በቀጥታ ለቦርድ መቅረቡንም እንደሚቃወም ተናግሯል፡፡
ማኅበሩ የተከለከላቸውን ጥቅሞችና መብቶች ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ አለመግለጹን የገለጸው ሆቴሉ፣ መጠየቅ የሚገባውን ነገር ከሚገባው ቀን አንስቶ እስከ ስድስት ወራት ውስጥ ካልጠየቀ በይርጋ ቀሪ እንደሚሆን ጠቁሞ፣ ማኅበሩ መጠየቅ በሚገባው ወቅት ባለመጠየቁ መብቶቹ ወይም ጥቅሞቹ በይርጋ መቋረጣቸውን ገልጿል፡፡
የሠራተኞች ማኅበር የክሱ ፍሬ ቃል ሆቴሉ በኅብረት ስምምነት ላይ የተጠቀሱ የሠራተኞች መብቶችንና ጥቅሞችን ተግባራዊ ባለማድረጉ ተግባራዊ እንዲደረግ እንዲወሰንለት መጠየቁን ያስተወሰው ሆቴሉ፣ ማኅበሩ ላነሳቸው 12 ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ለሠራተኞች የሥራ ዝርዝር እንዳልተሰጠ ቢገልጽም ሆቴሉ አስፈርሞ መስጠቱን፣ የአደጋ መከላከያ ትጥቆችንም መስጠቱን ገልጾ፣ የሠራተኞች ማሻሻያ የትምህርት ክፍያ 250 ሺሕ ብር ክፍያን በሚመለከት፣ የአፈጻጸም ፖሊሲ ሪፖርት አርቅቆ ቢያቀርብም ማኅበሩ ምላሽ አለመስጠቱን፣ ነገር ግን ለሚማሩ ሠራተኞች ሆቴሉ ሳያቋርጥ እየከፈለ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በሆቴሉ ለሚፈጸም ጥፋት ላይ ምርመራ ሲደረግ ማኅበሩ በታዛቢነት አለመሳተፉ በማኅበሩ የቀረበው ክስ በጅምላና ያለተጨባጭ የቀረበ በመሆኑ ውድቅ ሊደረግ እንደሚገባ ገልጾ፣ ማሳተፉን የሚገልጽ ማሳያም ማቅረቡን በመልሱ ጠቅሷል፡፡ ቦነስን በሚመለከት ማኅበሩ ሳያውቅ የሰጠው ነገር እንደሌለ ገልጾ፣ ልዩ ማበረታቻ ስጦታ የሆቴሉ ስለሆነ ማኅበሩን እንደማይመለከት አስታውቋል፡፡ የውጭ ኦዲተር ሪፖርትን በሚመለከት ማስረጃ መስጠቱን፣ በክፍት የሥራ ቦታ ውድድር ላይ ማስታወቂያ እንደሚለጥፍ፣ አመቺ መንገድ ላላቸው የሌሊት ሽፍት ሠራተኞች የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ የዓመት ፈቃድ፣ የሕመምና የጋብቻ ፈቃድ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት እየሰጠ መሆኑን በመጠቆም ክሱን ተቃውሟል፡፡
ከወሊድ የሕክምና ወጪ ሦስት ሺሕ ብር ላይ የገቢ ግብር ተቀንሶ እንደማያውቅ፣ የመድን ዋስትና ፖሊሲን በሚመለከት ለቀድሞው የሠራተኛው ማኅበር ሊቀመንበር አቶ መስፍን ምትኩ መስጠቱንና በሳምንት ከ48 ሰዓታት በላይና በቀን ከስምንት ሰዓታት በላይ እንዲሠራ የተደረገ ሠራተኛ አለመኖሩን ሆቴሉ በሰጠው የመቃወሚያ መልስ ለቦርዱ አስረድቷል፡፡ ማኅበሩ በቀላሉ ተቀራርቦና ተነጋግሮ መፍትሔ ማግኘት ሲቻል፣ ሙግትን እንደተሻለ አማራጭ በመቁጠር ጥቃቅን ጉዳዮችን ይዞ ወደ ክርክር በመቅረቡ ሆቴሉ ማዘኑን በመቃወሚያ መልሱ ጠቁሟል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የተከሳሾችን አቤቱታ ተቀብሎ ሆቴሉ መልስ እንዲሰጥ ባዘዘው መሠረት ሆቴሉ መልስ ቢሰጥም፣ በመልሱ ላይ ክሱን የማየት መብት እንደሌለው በመጥቀሱ፣ “ቦርዱ ሥልጣን አለው ወይስ የለውም?” በሚለው ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 7 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment