Tuesday, June 11, 2013

የአርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት በከባድ የማታለል ወንጀል ተጠርጥረው ተከሰሱ


• ዋና ጸሐፊውና የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊው ተካተዋል
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር አባላት ለሆኑና በአዲስ አበባ ለሚኖሩ አቅመ ደካማ አርበኞች የሰጠውን ኮንዶሚኒየም ቤት ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል የተጠረጠሩት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት፣ ዋና ጸሐፊና የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ በከባድ የማታለል ወንጀል ተከሰሱ፡፡ 
በከባድ የማታለልና ጉዳት የማድረስ ወንጀል ተጠርጥረው በፌደራል ዓቃቤ ሕግ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ክስ የተመሠረተባቸው የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ሊቀ ትጉሀን አስታጥቄ አባተ፣ ዋና ጸሐፊው አሥር አለቃ ሰጥአርጌ አያሌው፣ የአስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊው አቶ በቀለ ሻረው ናቸው፡፡ 
በተጠርጣሪዎቹ ላይ ዓቃቤ ሕግ ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ለፍርድ ቤቱ ያቀረበባቸው ክስ እንደሚያብራራው፣ ግንቦት 16 ቀን 1998 ዓ.ም. እና ከዚያ በፊት ቀኑ ባልታወቀ ጊዜ የአስተደደሩ ከንቲባ በአዲስ አበባ ለሚኖሩና አቅመ ደካማ የማኅበሩ አባላት የኮንዶሚኒየም ቤት እንዲሰጣቸው አዘዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ያንን መሠረት በማድረግ ፕሬዚዳንቱና ዋና ጸሐፊው የራሳቸው ቤት እያላቸው የሌላቸው መስለው በመቅረብና አስተዳደሩን በደብዳቤ በመጠየቅ፣ አቅም ለሌላቸው ሊሰጥ የነበረውን ስፋቱ 48.19 ካሬ ሜትር ባለአንድ መኝታ ቤት ሁለቱም መውሰዳቸውን ክሱ ይገልጻል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ሥልጣናቸውን አላግባብ በመጠቀም በወቅቱ የአስተዳደሩ ከንቲባ የነበሩት አቶ አርከበ እቁባይ፣ ለአቅመ ደካማ አርበኞች እንዲሰጥ ትዕዛዝ ከሰጡባቸው ኮንዶሚኒየም ቤቶች፣ አርበኞች ያልሆኑ የፕሬዚዳንቱና የዋና ጸሐፊው ዘመዶችን ጨምሮ ለ11 ግለሰቦች እንዲሰጥ ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አመልክቷል፡፡
በፕሬዚዳንቱ አዛዥነትና በዋና ጸሐፊው ደብዳቤ አዘጋጅነት አርበኛ ላልሆኑ ግለሰቦች የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አርከበ ዕቁባይ አቅመ ደካማ ለሆኑና ኪራይ መክፈል ለማይችሉ 25 ቤቶች በነፃ እንዲሰጣቸው ካዘዙት ውስጥ አርበኛ ላልሆኑ ሁለት ግለሰቦች መስጠት፣ አርበኛ ላልሆኑና ደቡብ ክልል ዳውሮ ዞን ውስጥ አባት አርበኞች እንደሆኑ በማስመሰል ገንዘብ ወጪ አድርገው ገንዘቡ አርበኛ በሆኑ፣ ግን ፊርማቸው የእነሱ ባልሆነ ስም ወጪ በማድረግ መጠርጠራቸውን ክሱ ያትታል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለምክትል ፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ በመጻፍ ለማኅበሩ ብድር ሲጠይቁ፣ ዋና ጸሐፊው ብድር መሆኑ ቀርቶ በደመወዝ ጭማሪ እንዲሆን በመቀየር ገንዘቡን እንዲወስዱ ማድረጋቸውንም ክሱ ያክላል፡፡
ፕሬዚዳንቱና ዋና ጸሐፊው ባላቸው ሚስጥራዊ ግንኙነት አንዱ አንዱን በመወከል ገንዘብ ወጪ እንዲሆን በማድረግ በ2004 ዓ.ም. በጀት ዓመት የማኅበሩ ካፒታል በኦዲት ሲመረመር፣ 98,569.43 ብር ልዩነት መገኘቱን የዓቃቤ ሕግ ክስ ያብራራል፡፡
ያላግባብ የገንዘብ አወጣጥ፣ የአበል አከፋፈል፣ ማኅበሩ ሕንፃ በማከራየት ከሚያገኘው ገቢ የገቢ ግብር ባለመክፈል፣ ገቢን አሳንሶ ማሳወቅ፣ ጊዜን ጠብቆ አለመክፈል፣ ለከፍተኛ ወጪ በመዳረጋቸውና በሌላ ሰው ጥቅምና ሥራ አመራር ላይ ከባድ ጉዳት ማድረስ ወንጀል ተጠርጥረው መከሰሳቸውን የክስ ቻርጁ ይገልጻል፡፡
ዓቃቤ ሕግ ክሱን ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አምስተኛ ወንጀል ችሎት ያቀረበ ቢሆንም፣ ሁለተኛ ተከሳሽ አሥር አለቃ ሰጥአርጌና አቶ በቀለ ሻረው ሲቀርቡ፣ ፕሬዚዳንቱ ሊቀ ትጉሀን አስታጥቄ አባተ ባለመቅረባቸው ክሱ እንዳይነበብ፣ የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ማረሚያ ቤት ቆይተው ፕሬዚዳንቱ ሲቀርቡ እንዲቀርቡ አመልክቶ ነበር፡፡
ፕሬዚዳንቱ በሕመም ምክንያት እንዳልቀረቡ ጠበቃቸው ቢገልጹም፣ ፍርድ ቤቱ በሌለ ተጠርጣሪ ተከሳሽ ላይ ጠበቃ መናገር እንደማይችል በመግለጽ፣ የሁለተኛና የሦስተኛ ተከሳሾች ስምና አድራሻ በመመዝገብ ስለ ክሱ የሚሉት ካለ ጠይቋቸው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ዋና ጸሐፊው የ83 ዓመት አዛውንት ሲሆኑ፣ አስተዳዳሪውና የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊው የ64 ዓመት አዛውንት መሆናቸውንና የቤተሰብ ኃላፊ በመሆናቸው የዋስትና መብታቸው እንዲጠበቅላቸው ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ በሰጠው ብይን ዋና ጸሐፊውና የአስተዳደርና የጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊው እያንዳንዳቸው በ25 ሺሕ ብር ዋስ እንዲለቀቁ ብይን ሰጥቷል፡፡ ፕሬዚዳንቱን ፖሊስ አስሮ ለሰኔ 21 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲያቀርብም አዟል፡፡   

No comments:

Post a Comment