Tuesday, June 11, 2013

የሙስና ወንጀል ተጠርጣሪዎች ከ90 በላይ ተሽከርካሪዎች ታገዱባቸው 

ከ50 በላይ ተሽከርካሪዎች የአንድ ተጠርጣሪ ናቸው ተብሏል
ከግንቦት 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በከባድ ሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ከኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በቁጥጥር ሥር የዋሉ ነጋዴዎች፣ ከ90 በላይ ተሽከርካሪዎች እንደታገዱባቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
የአብዛኛዎቹን ተጠርጣሪዎች የባንክ ሒሳብ ያሳገደው የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን መርማሪ ቡድን እስካለፈው ዓርብ ድረስ በተጠርጣሪዎቹ፣ በቤተሰቦቻቸው፣ በንግድ ድርጅቶቻቸውና በተለያዩ ሁኔታዎች ተመዝግበው የሚገኙ ተሽከርካሪዎቹን ማሳገዱን ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ 
በእስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪዎች ተሽከርካሪዎቻቸው የታገዱ መሆናቸውን የገለጹት ምንጮቹ፣ ከ50 በላይ የሚሆኑት ተሽከርካሪዎች ስማቸው ያልተጠቀሰ የአንድ ተጠርጣሪ ንብረት መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
ከቤት አውቶሞቢል እስከ ተሳቢ የጭነት ተሽከርካሪዎች መታገዳቸውን የገለጹት ምንጮች፣ የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በተጠርጣሪዎቹ ላይ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ለመሰብሰብ ባደረገው እንቅስቃሴ ሌሎች ተጨማሪ ንብረቶችን ማግኘቱንም አስረድተዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ ተጨማሪ ማስረጃዎች ያላቸው የተሠሩ ቤቶች፣ ካርታ የተሠራላቸው መሬቶችና ሌሎችን ንብረቶችን በሚመለከት፣ የኮሚሽኑ ኃላፊዎች ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኃላፊዎች ጋር እየተወያዩበትና እየተመካከሩበት መሆኑን ምንጮቹ ጠቁመዋል፡፡
መርማሪ ቡድኑ የተጠርጣሪዎቹ የባንክ ሒሳብ እንዲታገድ በማድረጉ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ እንዳይንቀሳቀስ ሳያደርግ እንደማይቀር ምንጮች ግምታቸውን አስረድተዋል፡፡
የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን ፍርድ ቤት አቅርቦ የጊዜ ቀጠሮ የጠየቀባቸው ተርጣሪዎች 59 ሲሆኑ፣ አንዱ ተጠርጣሪ ግን መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment