መንግስት አባይን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረጉን እንዲያቆም አንድነት አሳሰበ
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የኢትዮጵያ መንግስት የአባይን ጉዳይ የፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረጉን እንዲያቆም አሳሰበ፡፡
አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) “ሁሉንም ነገር ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል የቆረጠ ፓርቲ የሀገርን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ መጣሉ የማይቀር ነው” በሚል ርዕስ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እንደገለፁት አባይ ከመገደቡ በፊት መፈፀም የሚገባው የዲፕሎማሲ ስራዎች አልተሰሩም፡፡
“በአባይ ላይ ግድብ ከመሰራቱ በፊት ማለቅ የሚገባቸው የዲፕሎማሲ ስራዎችና ሌሎች ጉዳዮች በውል ታይተዋል ወይ የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢ ነው፡፡ ከነዚህም ዋነኛው በቂ የዲፕሎማሲ ስራ ያለመሰራቱና ከአባይ ተጋሪ ሃገሮች ጋር በቂና አስተማማኝ ውይይት አድርጎ ስምምነት አለመድረስ በዚህ የተነሳ ሃገሪቱ የጦርነት ስጋት ቢገጥማት ለመቋቋም በቂ ዝግጅት ያለማድረግ ይገኙበታል፡፡”
አንድነት በመግለጫው የኢትዮጵያና የግብፅ መንግስት ከፀብ አጫሪ ድርጊት ተቆጥበው በጠረጵዛ ዙሪያ ንግግሮች ላይ እንዲያተኩሩ አሳስቧል፡፡
ሁለቱም ሀገሮች የአባይን ጉዳይ ለውስጥ ፓለቲካ ማብረጃ ከማድረጋቸው እንዲቆጠቡና የኢትዮጵያ መንግስት ደግሞ ጉዳዩን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ማድረጉን እንዲያቆም ጠይቀዋል፡፡
ገዥው ፓርቲና መንግስት በህዳሴው ግድብ ላይ ህዝቡን ባለቤት አላደረጉም ብሏል አንድነት በመግለጫው፡፡
“ችግሩ የሚመነጨው ገዥው ፓርቲ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ ለመስራት መነሳቱ ሳይሆን የአባይን ጉዳይ የኢሕአዴግ ጉዳይ ማድረጉ፤ የአባይን ጉዳይ የአንድ ግለሰብ ራዕይ ማድረጉና ከእለት ጉርሱ ቀንሶ ቦንድ እየገዛ ያለውን ህዝብ የግድቡ ባለቤት ማድረግ አለመቻሉ ነው፡፡ ግድቡ የኢትዮጵያ ህዝብ ግድብ ይሁን የኢሕአዴግ በዉል አልለዩትም፡፡”
source ERTA
No comments:
Post a Comment