አሠልጣኝ ሰውነትና ስብስባቸው በጥንካሬው ዘልቋል
- እሑድ በደቡብ አፍሪካ ይፈተናል
አስተማማኝ መሠረት እንደሌለው የሚነገርለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በርቀት የውጤት ብርሃን መመልከት ጀምሯል፡፡ በዚህም ለዓመታት ለባእድ እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴ ውድ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ፣ እንዲያም ሲል ጐራ ለይተው ለመጐዳዳት ሲፈላለጉ የቆዩ የእግር ኳስ ቤተሰቦች በአሁኑ ወቅት በአንድ መድረክ ስለአገራቸው እግር ኳስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታና ውጤት መነጋገር ጀምረዋል፡፡
አስተማማኝ መሠረት እንደሌለው የሚነገርለት የኢትዮጵያ እግር ኳስ በርቀት የውጤት ብርሃን መመልከት ጀምሯል፡፡ በዚህም ለዓመታት ለባእድ እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴ ውድ ጊዜያቸውን ሲያጠፉ፣ እንዲያም ሲል ጐራ ለይተው ለመጐዳዳት ሲፈላለጉ የቆዩ የእግር ኳስ ቤተሰቦች በአሁኑ ወቅት በአንድ መድረክ ስለአገራቸው እግር ኳስ ቀጣይ ዕጣ ፈንታና ውጤት መነጋገር ጀምረዋል፡፡
ለሦስት አሠርታት ያህል ከአህጉራዊም ሆነ ከዓለም አቀፍ መድረክ ተገልሎ በ‹‹ነበር›› የቆየው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪኩን ከቀየረበት ከዘንድሮው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ በኋላም ለ2014 የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድቡን እየመራ ይገኛል፡፡
በአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ከሜዳው ውጪ ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዞ መመለስ የማይገፋ ዳገት ሆኖበት ቢቆይም በአሁኑ ወቅት ግን የነበረውን ዓይነ ጥላ ታሪክ አድርጐ ተመልሷል፡፡ ይህንኑ ተከትሎ አገሪቱን ‹‹የሯጮች ምድር›› ብለው የሚያውቋት ትላላቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን በተወሰነ መልኩም ቢሆን፣ በአሁኑ ወቅት ስለአገሪቱ እግር ኳሳዊ እንቅስቃሴ ማውራት ጀምረዋል፡፡ ሰሚ አግኝቶ ፈጻሚና አስፈጻሚ አካልና ተቋም ካለ ደግሞ እንደ አትሌቲክሱ ሁሉ እግር ኳሱም ፍሬ አፍርቶ የሚታይበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆን ሙያተኞች እምነታቸው መሆኑን እየገለጹ ናቸው፡፡
እንደ ሙያተኞቹ፣ ይህ የሚሆነው የየተቋማቱን መደርደሪያ ያጨናነቁ ‹‹የዳሰሳ ጥናት›› ውጤቶች ሪፖርቶችን ከማጠናከር አልፈው ወደ መሬት ወርደው መተግበር ሲችሉ ብቻ ስለመሆኑ ጭምር ያምናሉ፡፡
የአሠልጣኝ ሰውነት ስብስብ፣ አገሪቱ ከመሠረተችው የአፍሪካ ወንጫ ተፎካካሪነት ርቃ፣ የሩቅ ተመልካች ከሆነች ከ31 ዓመት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫም ሆነ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ምድብ ድልድል ተስፋ ሰጪ ጉዞ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይኼው ተስፋ ሰጪ ጅምር ከብሔራዊ ቡድኑ አልፎ ለአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ስምንቱ ውስጥ መግባት የቻለው የአንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሳትፎ በርቀት ለሚታየው የውጤት ብርሃን ማረጋገጫ ስለመሆኑም የሚናገሩ አሉ፡፡
ባለፈው ቅዳሜ ከቦትስዋና አቻው ጋር የተጫወተው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን ጌታነህ ከበደና ሳላዲን ሰይድ ባስቆጠሯቸው ግቦች 2ለ1 አጠናቆ ተመልሷል፡፡ ውጤቱም የምድብ መሪነቱን በሁለት ነጥብ ልዩነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አስችሎታል፡፡
ውጤቱን ተከትሎ በርካታ መገናኛ ብዙሀን ለዓመታት በውጤት ቀውስ ሲቆዝም ለኖረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ መነቃቃት ይችል ዘንድ አጋጣሚው መልካም ስለመሆኑ ጭምር ምስክርነት የሚሰጡ እንዲበረክቱ አድርጓል፡፡
በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድበ አንድ ከደቡብ አፍሪካ፣ ቦትስዋናና ማዕከላዊ አፍሪካ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ ብራዚል ለምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ትኬት ከመቁረጡ አስቀድሞ ለሚጠብቀው አንድ የደርሶ መልስ ጨዋታ ዕድሉን ለመወሰን የፊታችን እሑድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ደቡብ አፍሪካን ያስተናግዳል፡፡
ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ ማን የተሻለ ዕድል ይኖረዋል ለሚለው ለሁለቱ ቡድኖች እንቅስቃሴ የተመደበውን ዘጠና ደቂቃ መጠበቅ የግድ መሆኑ ባያጠራጥርም፣ ነገር ግን እንደ በርካታ ዘገባዎች ከሆነ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታውን በሜዳውና በደጋፊው ፊት የሚያደርግ በመሆኑ ከምድቡ አንደኛ ሆኖ ለማለፍ ሰፊ ዕድል እንዳለው ቅድመ ግምታቸውን የሰጡ በርካታ ናቸው፡፡ ዘገባዎቹ ለቅድመ ግምታቸው ማጠናከሪያ የሚሉት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሁን ከሚገኝበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ሆነ ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎው አስቀድሞ የስኬት ጉዞውን የጀመረው፣ የሱማሊያ አቻውን ጂቡቲና አዲስ አበባ ስታዲየም ካደረጋቸው የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ጀምሮ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡
ቡድኑ የሱማሊያ አቻውን ምንም እንኳ በመጀመሪያው ጨዋታ ጂቡቲ ላይ 0ለ0 ተለያይቶ አዲስ አበባ ላይ 5ለ0 ያሸነፈ ቢሆንም፣ ከዚያ በኋላ ባደረጋቸው ጨዋታዎች የነበሩበትን ክፍተቶች ከቀን ወደ ቀን በማረም የመጣበት መንገድ ተጠቃሽ ሆኗል፡፡
አስከትለውም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ አስተናጋጅነት በተከናወነው የአፍሪካ ዋንጫ ከምድብ ማጣሪያው ማለፍ ባይችልም፣ ነገር ግን ከመድረኩ ርቆ ከቆየበት ዓመታት አኳያ ወደ ትክክለኛው ትራክ ለመግባት እየተከተለው ያለው እንቅስቃሴና አቅጣጫ የእግር ኳሱ ዕድገት ምልክት ስለመሆኑም የሚናገሩ አሉ፡፡
ይኼው እምነት ያደረባቸው በርካታ የእግር ኳሱ ቤተሰቦች በበኩላቸው፣ ዋሊያዎቹ በማስመዝገብ ላይ የሚገኙት ውጤት የአገሪቱ እግር ኳስ ስፖርት ቀድሞ ይታይበት ከነበረው መቀዛቀዝ እየተነቃቃ መሆኑን ነው ይላሉ፡፡
በተያያዘ፣ የፊታችን እሑድ በአዲስ አበባ ስታዲየም ወሳኝ ጨዋታ የሚጠብቀው የደቡብ አፍሪካ ቡድን ከነገ በስቲያ ዓርብ አዲስ አበባ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ ጨዋታውን የሚመሩት ዳኞች ደግሞ አራቱም ከግብፅ መሆናቸው ታውቋል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ጎርደን ኢግሰንድ አዲስ አበባ ላይ ለሚጠብቃቸው ወሳኝ ጨዋታ መዘጋጀተቸውን ገልጸው፣ በሌላ ወገን ደግሞ ከተጋጣሚያቸው የሚጠብቃቸው ፈተና ቀላል እንደማይሆን ጭምር ተናግረዋል፡፡ ደቡብ አፍሪካና ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ሰኔ 23 ቀን 2004 ዓ.ም. በምድብ ማጣሪያው የመጀመሪያ ጨዋታ ደቡብ አፍሪካ ላይ በረስተንበርግ ስታዲየም 1ለ1 መለያየታቸው ይታወሳል፡፡
እንደ አሠልጣኙ ሁሉ ደቡብ አፍሪካውያን፣ ቡድናቸው አዲስ አበባ ላይ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሚጠብቀው ግጥሚያ ምናልባትም የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ጉዞ ሊገታ እንደሚችል ጭምር ሥጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል፡፡
ቦትስዋናን በሜዳዋ 2ለ1 የረታው የአሠልጣኝ ሰውነት ቢሻው ስብስብ ትናንት ጠዋት ላይ አዲስ አበባ ገብቶ፣ ከሰዓት በኋላ የመጀመሪያውን ልምምድ በአዲስ አበባ ስታዲየም አድርጓል፡፡
No comments:
Post a Comment