ዜግነት ያልቀየሩ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ምርጫ እንዲሳተፉ ሊደረግ ነው
ዜግነት ያልቀየሩ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገሪቱ በሚካሄዱ ምርጫዎች በያሉበት ሆነው መሳተፍ እንዲችሉ በዳያስፖራ ፖሊሲ ድጋፍ ሊያገኙ ነው፡፡
ዳያስፖራው በአገሩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ
እንቅስቃሴዎች በንቃት እንዲሳተፍ ለማስቻል የተቀረውና የፊታችን ቅዳሜ ሰኔ 8 ቀን 2005 ዓ.ም. መፅደቁ ይፋ
የሚሆነው የዳያስፖራ ፖሊሲ፣ ዳያስፖራው በተደጋጋሚ ሲያነሳ የነበረውን በምርጫ የመሳተፍ መብት መደገፉ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሆነው በምርጫ እንዲሳተፉ የሚያስችል አሠራር በፖሊሲው በማካተትና በማፅደቅ የኢሕአዴግን መንግሥት የመጀመርያው ያደርገዋል ተብሏል፡፡
በታህሳስ 2005 ዓ.ም. በፀደቀው የዳያስፖራ ፖሊሲ ተግባራዊነት ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዳያስፖራው ጋር ለመምከር መዘጋጀቱን አስመልክቶ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ የተገኙት የዳያስፖራ ተሳትፎ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ሙሉጌታ ከሊል እንደተናገሩት፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜግነታቸውን እስካልቀየሩ ድረስ በያሉበት ሆነው በኢትዮጵያ በሚካሄዱ ምርጫዎች የመሳተፍ መብታቸውን ፖሊሲው አረጋግጧል፡፡
በዳያስፖራ ፖሊሲው ዳያስፖራው በዲሞክራሲያዊ ሒደት የሚኖረውን ተሳትፎ አስመልክቶ በተቀመጠው አንቀጽ መሠረት፣ በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ዜጐች የምርጫ ሕጉ በሚፈቅደው መሠረት በምርጫ እንዲሳተፉ ምርጫ ቦርድ ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ የሎጂስቲከስ ችግሩንም ከዳያስፖራው ጋር በመተባበር ይፈታል ተብሏል፡፡
በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ውይይቶች ሲደረጉ ዳያስፖራው በተደጋጋሚ ያነሳ የነበረው በፋይናንስ ማለትም በባንክና በኢንሹራንስ ዘርፍ የመሳተፍ ጥያቄ ግን ጥናት የሚጠይቅ በመሆኑ ለጊዜው በፖሊሲው አልተካተተም፡፡ አቶ ሙሉጌታ እንዳሉት፣ በባንክና በኢንሹራንስ ዘርፍ ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ለማሰማራት የሚያስችለው ጥናት በብሔራዊ ባንክ በኩል እየተጠና ነው፡፡ የፀደቀው ፖሊሲ የዳያስፖራውን በፋይናንስ ተሳትፎ የመሰማራት ዕድል ባያካትተውም፣ ብሔራዊ ባንክ በመመርያው ውስጥ ካስገባው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም በፖሊሲ ማሻሻያው ውስጥ ያካትተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment