Tuesday, June 11, 2013

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ መዝገብ ተለዋጭ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ሰጠ

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ መዝገብ ተለዋጭ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ሰጠ 

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በፌዴራሉ ሥነ ምግባርና ፀረ - ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል በእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ መዝገብ ተለዋጭ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ሰጠ፡፡
የፍርድ ቤቱ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ሰኔ 3/2005 ዓ.ም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ግለሰቦችን በተመለከተ የፌዴራሉ ሥነ ምግባርና ፀረ - ሙስና ኮሚሽን የምርመራ ቡድን በእነ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ መዝገብ ተጠርጥረው ከተያዙት 12 ግለሰቦች መካከል ሁለቱ በዋስ መለቀቃቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልጿል፡፡
የምርመራ ቡድኑ ለፍርድ ቤቱ እንደገለጸው በመዝገቡ ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ከነበሩት መካከል 11ኛ እና 12 ተከሳሽ አቶ ሃብቶም ገብረመድህንና ወይዘሮ ንግሥቲ ተስፋዬ በዋስ መለቀቃቸውን ገልጿል፡፡ በዋስ የተለቀቁት የአቶ ገብረዋህድ ባለቤት እህትና ልጅ ናቸው፡፡  
ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ምርመራ ለማድረግ የጠየቀውን የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ በተመለከተ የግራና ቀኙን ክርክር ሲያዳምጥ ውሏል፡፡
ፍርድ ቤቱ በቅድሚያ የምርመራ ቡድኑ ባለፉት 14 ቀናት ያከናወነውን ምርመራ በተመለከተ የምርመራ ቡድኑ ያከናወናቸውንና ያላከናወናቸውን ተግባራት አዳምጧል፡፡
የምርመራ ቡድኑ በምርመራው በርካታ ሥራዎችን ማከናወኑንና ከእነዚህም መካከል ከአራጣ ብድር ጋር በተያያዘ የተቋረጡ ክሶችን፣ ከአንድ የአራጣ ብድር ጋር በተያያዘ የኦዲት ሪፖርትና የ50 ሚሊዮን ብር አራጣ ብድር የሚመለከት ማስረጃዎችን ከባንክ ማሰባሰቡን ገልጿል፡፡
እንዲሁም ከቀረጥ ነጻ የገቡ የ10 ሆቴሎች የግንባታ ዕቃዎች ለታለመላቸው ዓላማ አለመዋላቸውን፣ በፍራንኮ ቫሉታ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገባ የተከለከለ ሲሚንቶ በተመለከተ የሰነድ ማስረጃና በኮንትሮባንድ የገባ የሕክምና ዕቃ በተመለከተ ማስረጃ ማሰባሰቡን አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም በጅምላ ከተቋረጡ 60 መዝገቦች 4ቱን ሰብስቦ መመርመሩን፣ ለጠቋሚ የሚከፈል የተመዘበረ የመንግስትን ገንዘብ በተመለከተ ማስረጃ ማሰባሰቡን፣ በርካታ የሙያና የዓይን ምስክሮችን ቃል መቀበሉን ለፍርድ ቤቱ አስታውቋል፡፡
የምርመራ ቡድኑ ይቀሩኛል ካላቸው የምርመራ ሥራዎች መካከል የኦዲት ሥራ፣ ቀሪ የሰነድና የሰው ማስረጃ ማሰባሰብ፣ የምሥክር ቃል መቀበል፣ የተሰወሩ የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ የሚሉት ይገኙበታል፡፡
የምርመራ ሥራው ሰፊና ውስብስብ መሆኑንና ከአዲስ አበባ ውጪ በመግቢያና መውጫ ጣቢያዎች በኮንትሮባንድ የሚገቡ ዕቃዎችን በተመለከተ ማስረጃ የማሰባሰብ ሥራ እየተሰራ ቢሆንም ቀሪ ሥራዎች ይቀራሉ ብሏል፡፡
በመሆኑም እነዚህን ሰፊና ውስብስብ የምርመራ ሥራዎች ለማከናወን ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው ለፍርድ ቤቱ አመልክቷል፡፡   
ፍርድ ቤቱ በመቀጠል በእነ አቶ ገብረዋህድ ወልደጊዮርጊስ መዝገብ የ10ሩ ተጠርጣሪዎች ጠበቆችና ተጠርጣሪዎቹ ያቀረቡትን የመከራከሪያ ሃሳብ አዳምጧል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆችና ተጠርጣሪዎቹ ለምርመራ ቡድኑ ቀደም ሲል የ28 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ስለተሰጠውና ከደንበኞቻቸው የሚፈለጉ ማስረጃዎች የተሰበሰቡ በመሆናቸውና ቀሪዎቹ የምርመራ ሥራዎች ተጠርጣሪዎቹን የማይመለከቱ በመሆናቸው የቀረበው የጊዜ ቀጠሮ ሊፈቀድ አይገባም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡
አንዳንድ ተጠርጣሪዎች ቤታቸውም ሆነ መኖሪያ ቤታቸው ተፈትሾ ምንም ዓይነት ማስረጃ ስላልተገኘ የዋስትና መብታችን ሊጠበቅልን ይገባል ብለዋል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ - ሙስና ኮሚሽን ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥራ ያዋለው በቂ ማስረጃዎችን በማሰባሰብ መሆኑንና ደንበኞቻቸው ሊያጠፉት የሚችሉት ማስረጃ ስለሌለ የዋስ መብታቸው እንዲጠበቅ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል፡፡  
ፍርድ ቤቱ የተጠርጣሪዎችንና የጠበቆቻቸውን የመከራከሪያ ሐሳብ ካዳመጠ በኋላ የምርመራ ቡድኑ አስተያየት እንዲሰጥበት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የምርመራ ቡድኑም የሙስና ወንጀሉ የተፈጸመው በፌዴራል ጉምሩክና ገቢዎች ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ የሥራ ኃላፊዎችና ከፍተኛ ነጋዴዎች በአባሪና በተባባሪነት በመመሳጠር መሆኑን ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱ የግራና ቀኙን ክርክር ካደመጠ በኋላ የምርመራ ቡድኑ ያቀረበውን ተጨማሪ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጥያቄ በመቀበል ለሰኔ 17 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡




No comments:

Post a Comment