Tuesday, October 15, 2013

 የአዲስ አበባውን የፈንጂ ፍንዳታ ያደረሱት ሁለት ሶማሊያውያን አሸባሪዎች መሆናቸውን ፖሊስ ገለፀ

በአዲስ አበባ  ቦሌ  ክፍለ ከተማ  የደረሰው የፈንጂ ፍንዳታ በሁለት ሶማሊያውያን  አሸባሪዎች የተፈፀመ መሆኑን የኢትዮጵያ  ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ገለፀ ።
የኢትዮጵያ  ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል አሰፋ አብዩ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳስረዱት ፥ በክፍለ  ከተማው ወረዳ 01 ቀበሌ 01 በተለምዶ ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ  በአንድ የመኖሪያ ቤት  ውስጥ ነው ፍንዳታው የደረሰው ።
ፖሊስ ፍንዳታው ፈንጂ መሆኑንና ፥  በጥቅም ላይ የዋለው ቲ ኤም ቲ የተባለ  የፈንጂ ዓይነት መሆኑን እንደደረሰበት  ገልፀዋል ።
ፍንዳታውንም  ሁለት  ሶማሊያውያን ማቀነባበራቸውን ፖሊስ እንዳረጋገጠና  ግለሰቦቹ የአሸባሪ ቡድኑ አልሸባብ አባል መሆናቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሉም ነው ጀነራል አሰፋ አብዩ ያስረዱት ።
ከሁለቱ  አሸባሪዎች መካከል አንደኛው ወገቡ ላይ የታጠቀና ለአጥፍቶ ጠፊ ተግባር የተዘጋጀ መሆኑን  የሚያሳይ ነው ።
ሌላኛው  አሸባሪ በሻንጣ ፈንጂ  የያዘ ሲሆን ፥ የፈነዳውም ፈንጂ በሻንጣው ውስጥ የነበረ መሆኑን ነው ጀነራል አሰፋ ያስረዱት ።
ለአጥፍቶ  ጠፊ ተግባር  ሲዘጋጅ የነበረው ግለሰብ የታጠቀው ፈንጂ  ግን  እንዳልፈነዳ አመልክተዋል ።
አሸባሪዎቹ በአጠቃላይ  ሶስት ፈንጂዎችንም ይዘው ነበር ።
አሸባሪዎቹ ህዝብ ባለበት ስፍራ አደጋ ለማድረስ ተከራይተው በነበሩበት ቤት ውስጥ ሲዘጋጁ ፍንዳታው ደርሷል ብሎ ፖሊስ እንደሚጠረጥር ነው የጠቆሙት ።
ከአሸባሪዎቹ  ጋር ፖሊስ የእጅ ቦምቦችንና ሽጉጥ ከነጥይቱ  አግኝቷል ።

ከዚህ የምንማረው  
ጀነራል አሰፋ አብዩ እንደሚሉት ሶማሊያውያን አሸባሪዎቹ  ቤቱን ከተከራዩ ከ22  እስከ 23 ቀን ይሆናቸዋል ።
እስከ  ስድስት የሚደርሱ  ቤቶችን በከተማዋ  የሚያከራዩት የቤቱ ባለቤቶች  ስለነዚህ  ግለሰቦች ስምን ጨምሮ  ማንነታቸውን  እንደማያውቁ ነው የተደረሰበት ።
በመሆኑም ህብረተሰቡ ቤቱንም ሆነ  መኪናውን ሲያከራይ ስለተከራዩ ማንነት በቂ  እውቀት ይዞ ፥  መታወቂያና ፓስፖርት ተመልክቶ  መሆን  እንዳለበት ነው ያሳሰቡት ።
የሚያገኛቸውን መረጃዎች በአቅራቢያው ለሚገኝ የፖሊስ  ተቋም  መስጠት  ግዴታው መሆኑን በመረዳትም ፥  ሽብርተኝነተን ከፖሊስ ጎን  ሆኖ  እንዲከላከል ጥሪ አቀርበዋል ።

 

No comments:

Post a Comment