Monday, October 7, 2013


የአማርኛ አድማጭ ፈረንጆች ገጠመኝ

የአማርኛ አድማጭ ፈረንጆች ገጠመኝ


ምሽት ከሥራ መውጫ ሰዓት በኋላ ከፍተኛ የእግረኞችና የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በሚስተዋልበት ሰዓት ላይ ነው፡፡
መገናኛ ውኃ ልማት እየተባለ የሚሠራው ቦታ ላይ ታክሲው ተሳፋሪ ሲያወርድ አነስተኛ ሻንጣቸውን በእጃቸው የያዙ ቦርሳቸውንም በትከሻቸው ያነገቡ አዛውንት የውጪ አገር ዜጋ (ፈረንጅ) ታክሲ ውስጥ ገቡ፡፡ ወዲያው ታክሲው መንቀሳቀስ እንደጀመረ ሳይጠየቁ ለረዳቱ ሒሳብ አውጥተው ከፈሉ፡፡ ብሩን ያወጡት ቦርሳቸው ውስጥ ካለ ዋሌት ወይም የቦርሳቸው ኪስ ሳይሆን ብርና ሳንቲሞች ከያዘውና በብር ላስቲክ ከተጠቀለለው ስስ ፌስታል ውስጥ ነበር፡፡ 
ሴትየዋ ታክሲ ውስጥ ሲገቡ ጀምሮ እያንዳንዱን እንቅስቃሴያቸውን ስትከታተልና ከእሳቸው ጀርባ ተቀምጣ የነበረች ተሳፋሪ አጠገቧ ለተቀመጡ ተሳፋሪዎች እንዲሰማ ለማድረግ በሚመስል መልኩ ድምጿን ከፍ አድርጋ ‹‹አይገርምም አበሻ እኮ ኩሩ ነው፡፡ አሁን ዋሌት የሌለው፣ የሳንቲም ቦርሳ የሌለው አለ›› እያለች ፈረንጆች እንዴት ግራ የሚያጋቡ እንደሆኑ፤ ሴትየዋ ገንዘብ በስስ ፌስታል ቋጥረው መያዛቸው ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነገር መሆኑን መናገሯን ቀጠለች፡፡ ሴትየዋ ሻንጣ በመያዛቸው ኮንትራት ታክሲ መያዝ እንደነበረባቸውም አስተያየት የሰጠ ሰውም ነበር፡፡ 
አዛውንቷ ሒሳብ ሊከፍሉ ሲሉ ምንም ግር ያላቸው ነገር አልነበረም፡፡ ያለምንም ግራ መጋባት ከጎናቸው የነበረ ተሳፋሪን አልያም ረዳቱን ሳይጠይቁ ትክክለኛውን ሒሳብ አውጥተው ነበር የሰጡት፡፡ መልስ እንደሚኖራቸው እርግጠኛ በመሆንም ረዳቱ መልሳቸውን እንዲሰጣቸው እንደመጠበቅ ብለውም ነበር፡፡ ከዚህ አዛውንቷ ትንሽም ቢሆን ነገሮችን እንደሚያውቁ በተወሰነ መልኩ አንድ አንድ የአማርኛ መግባቢያ ቃላትን እንኳ ሊሰሙ እንደሚችሉ መገመት ይቻላል፡፡ መልስ ሲሰጣቸው እዚያችው ስስ ፌስታል ውስጥ ከትተው ፌስታሉን በብር ላስቲክ ጠምጥመው ከነበረችበት አኖሯት፡፡ በዚህ ላይም ሌላ አስተያየት በተሳፋሪዎች ተሰነዘረ፡፡ የፈረንጆች ለገንዘብ ዋጋ መስጠት ሳንቲሞቹን ሳይንቁ ተቀብለው መልሰው ቋጥረው ማስቀመጣቸው ለገንዘብ የሚሰጡትን ዋጋ እንደሚያሳይ ተወራ፡፡ ፊት ለፊት ስለሳቸው ይህ ሁሉ ሲወራ ሴትየዋ ምንም እንኳ የውጭ ዜጋ ቢሆኑ አማርኛ ሊሰሙ የሚችሉበት ዕድል እንዳለ ያሰበ ፈፅሞ ያለ አይመስልም፡፡ ይልቁንም አማርኛ አይሰሙም በሚል ድምዳሜ ስለ እሳቸው እንደልብ ይወራል፡፡ ታክሲው ትርፍ ጭኖ ስለነበር አያት ጋር ሲደርሱ ወራጅ እንዲኖር በመፈለግ ረዳቱ ወራጅ የለም ወይ? እያለ ደጋግሞ ቢጠይቅም የወረደው አንድ ተሳፋሪ ብቻ ነበር፡፡ ድልድይ ጫፍ ሲደርስም መልሶ ተመሳሳይ ጥያቄውን አቀረበ፡፡ ማንም አልወረደም፡፡ ይኼንን የተመለከተው ሾፌር ወደ ኋላ ዞር በማለት ለረዳቱ ‹‹ቀዮም አትወርድም? እሷም ድልድይ ልትገባ?›› አለው፡፡ 
እንደዚህ ያሉ አጋጣማዎች በታክሲ ላይ የበለጠ ሊስተዋሉ ቢችሉም በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ይታያሉ፡፡ ብዙ ኢትዮጵያውያን ፈረንጆች፣ አፍሪካውያን፣ ቻይናውያንና ሌሎችንም የውጭ አገር ዜጎች ሲመለከቱ አማርኛ አይሰሙም አይናገሩም ብሎ በማመን ያለምንም ጭንቀት ፊት ለፊት ስለሰዎቹ የፈለጉትን ያወራሉ፡፡ የሚነገረው ነገር እንደሁኔታው ጥሩም መጥፎም ሊሆን ይችላል፡፡ 
ዓለም አቀፍ በሆነ የባህልና የባለሙያ ልምድ ልውውጥ አዲስ አበባ ላይ ለአንድ ዓመት የቆዩ ሁለት አፍሪካውያን ታክሲ ውስጥ፣ ካፍቴሪያዎችና ሌሎችም ቦታዎች ላይ ‹‹ጦጣ›› ሲባል በተደጋጋሚ በመስማታቸው ቃሉን በመያዝ በመጨረሻ ኢትዮጵያዊ ጓደኞቻቸውን ጠይቀው ትርጉሙን የተረዱበትና ነገሩን ከዘረኝነት ጋር ያገናኙበት አጋጣሚ እንደነበር የገለጹልን አሉ፡፡ 
ሊሊያን ቱውክ ለሥራ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው እኤአ 2009 ላይ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እየሠራች ያለችው በበጐ አድራጎት ድርጅቶች ውስጥ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቷ በፊት ጀርመን ውስጥ ለአንድ ወር አማርኛ ቋንቋ ተምራለች፡፡ እዚህ ከመጣች በኋላ ደግሞ የግል አስተማሪ ቀጥራ ቋንቋውን አጥንታለች፡፡ በኢትዮጵያ በሚኖራት ቆይታ ከሰዎች ጋር የሚኖራትን ገንኙነት የተቀላጠፈ እንዲሁም ቆይታዋን ውጤታማ ለማድረግ ቋንቋውን ለመቻል ራሷም ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን ትናገራለች፡፡ ከዚህ በመነሳት ለመግባባት ያህል መሠረታዊ የንግግር አማርኛ እንደምትችል፤ የመስማት ችሎታዋ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ነው ብላ እንደምታምን ገልጻልናለች፡፡ 
በተለይም ሥራዋ ከሕፃናትና ከሴቶች ጋር የሚያገናኝ ስለሆነ አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥሟት ሕፃናትና ሴቶች እንግሊዝኛ የማይችሉ በመሆናቸው አማርኛ መናገር እንደሚያስፈልጋት ገልጻልናለች፡፡ የአማርኛ ቋንቋ ችሎታዋን እንዴት እንደምትመዝነው ባቀረብንላት ጥያቄ መልሷ ‹‹መነጋገር መግባባት እችላለሁ፡፡ የመስማት ችሎታዬ ደግሞ በጣም አሪፍ ነው፤›› የሚል ነበር፡፡ 
በተደጋጋሚ ሰዎች አማርኛ መናገር አትችልም ብለው በማሰብ እሷን በሚመለከት የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ስለ እሷም ሲያወሩ አዳምጣለች፡፡ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ቢባሉም አብዛኞቹ መልካም አስተያየቶች እንደሆኑ የምትናገረው ሊሊያን ‹‹ሀብታም ውሻ፣ የኔ ቆንጆ፣ እንትንሽ ያምራልና አግብተሻል ወይ›› ዓይነት ነገሮችን በተደጋጋሚ መስማቷን ገልጻልናለች፡፡ 
እሷ እንደምትለው አዲስ አበባ ላይ የሚቀመጡ ፈረንጆች ምንም እንኳ ለረዥም ጊዜ ቢቆዩ አማርኛ ብዙ አይናገሩም፡፡ በተቃራኒው ገጠር ላይ የሚሠሩ በዚያ እንግሊዝኛ የሚያናግራቸው ስለማይኖር በጥሩ ሁኔታ አማርኛ ይናገራሉ፡፡ ይህን ሐሳብ ስትገልጽ ሊሊያን ገጠር ለማለት አሁንም አሁንም ‹‹ክፍለ ሀገር›› ነበር የምትለው፡፡ 
እዚያው ባሉበት አማርኛ አይሰሙም ተብሎ ስለራሳቸው ሲወራ መስማት፣ የተለያየ አስተየየት ማድመጥ በጥቅሉ ዕለት በዕለት በርካታ የውጭ አገር ዜጎችን የሚያጋጥም ነገር ነው ብሎ እንደሚያምን አፍሪካ ኅብረት ውስጥ የሚሠራውና ኢትዮጵያ ውስጥ ከአራት ዓመት በላይ የቆየው ኡጋንዳዊው ካቴንዴ ሀሰን ነው፡፡ እሱ እንደሚለው ነገሩ በሥራ ቦታ ላይም እንኳ ያጋጥማል፡፡ የአማርኛ ችሎታው ደህና የሚባል እንደሆነ የሚናገረው ሀሰን በአብዛኛው ቋንቋውን የተማረው ከጓደኞቹ ነው፡፡ 
ታክሲ አዙሮ ሲመጣ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ለመግባት ሲሞክሩ ከፊት የነበረችን ፈረንጅ ተመልክቶ ‹‹እሷንማ በቁመት እበልጣታለሁ›› ብሎ ለጓደኞቹ ከተናገረ በኋላ ወደፊት በመሄድ አጠገቧ ሆኖ በዘዴ ለመለካካት ሲሞክር ነገሩን ስትሰማ የነበረችው ፈረንጅ ‹‹አትበልጠኝም›› ብላ በአማርኛ ስትናገር በማየቱ መደንገጡን የነገረን ወጣትም አለ፡፡ 
የምትሠራበት ድርጅት ካለው ፕሮጀክቶች መካከል የአንዱ ፕሮጀክት ተጠቃሚዎችን በአስተርጓሚ ስታነጋግር መጀመሪያ ራሷን በማስተዋወቅ ዕድሜዋ 34 መሆኑንና አለማግባቷን ገልጻ ነበር፡፡ ከተጠቃሚዎቹ መካከል ሁለቱ ያለማግባቷን ምክንያት ሲነጋገሩ ሰምታ የተወሰነ ነገር የተረዳችውና ለመግባባት ያህል አማርኛ የምታውቀው የውጭ አገር ዜጋዋ በአገሯ ዘግይተው እንደሚያገቡ አስተርጓሚው እንዲነግርላት በእንግሊዝኛ ጠይቃ ‹‹የማገባው ከአፋር ወይም ከጣንቋ አበርገሌ ነው›› ስትል ሁሉም ሰው ተገርሞ እንደነበር በማስታወስ የነገረን ቦታው ከነበሩ አስተርጓሚዎች አንዱ ነው፡፡ 
ማርታ ንጉሤ ላለፉት ሦስት ዓመታት ጀርመናውያንና ጃፓናውያንን ለረዥም ጊዜ አማርኛ ቋንቋ አስተምራለች፡፡ በሥራ ምክንያት እያቋረጡ እየቀጠሉም ቢሆን በትጋት ቋንቋውን ለማወቅ የሚሞክሩ የውጪ አገር ዜጎች ጥቂቶች እንዳልሆኑ ትናገራለች፡፡ ታስተምራቸው ከነበሩ ከጥቂት የውጭ አገር ዜጎች ጋር የጠበቀ ጓደኝነትም ጭምር መመሥረት የቻለችው ማርታ፣ ሰው አማርኛ አይሰሙም ብሎ በመደምደም ዘወትር አስተያየት ስለሚሰነዝር መንገድ ላይ፣ ታክሲ ውስጥና በሌሎችም ቦታዎች በተደጋጋሚ ‹‹እሰማለሁ›› የሚል መልስ እንደሚሰጡ ታስረዳለች፡፡ 
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም ለተወሰነ ጊዜ ለሥራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የውጭ አገር ዜጎች ከመምጣታቸው በፊት በተወሰነ መልኩ ቋንቋውን መማር እንደሚጀምሩ፤ ከመጡ በኋላም በተለያዩ ተቋማት አልያም የግል መምህር ቀጥረው መሠረታዊ ነገሮችን ለመማር የመሞከራቸው ነገር በስፋት እየታየ ነው፡፡ 
የውጭ ዜጎችን አማርኛ ቋንቋ ማስተማር በሰዓት እስከ 250 ብር መሆኑን የነገሩን ሲኖሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ 350 መድረሱን የገለጹልም አሉ፡፡ 
ፌስቡክ ድረ ገጽ ላይ ባለው ‘Whats Happening in Addis’ ቡድን ገጽ ላይ በውጭ አገር ዜጎች የሚጠየቅ የግል አማርኛ መምህር ጥያቄ ወይም የት ሄደን ቋንቋውን መማር እንችላለን? የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ይጻፋል፡፡ 
‹‹Addis all Around, Addis Ababa›› እና ሌሎችም መሰል ድረ ገጾች ላይ መሠረታዊ የአማርኛ የመግባቢያ ቃላት በተለያየ መልኩ ሰፍረው ይታያሉ፡፡ አማርኛ ቋንቋ የማወቅ የውጭ አገር ዜጎችን ፍላጎት ተከትለው የተከፈቱ የተለያዩ ድረ ገጾች የመኖራቸውን ያህል በዚሁ ረገድ የውጭ አገር ዜጎችን ያግዙ ዘንድ ተዘጋጅተው ለገበያ የቀረቡ መጻሕፍትም አሉ፡፡ እነዚህ መጻሕፍት ቡክ ወርልድ፣ ሜጋ መጻሕፍት መደብርና በሌሎችም ቦታዎች እንዲሁም አዟሪዎች እጅ ላይ ይገኛሉ፡፡ 
ያለውን ፍላጎትና አዋጭነት አይቶ ሜጋም እነዚህን መጻሕፍት አሳትሟል፡፡ በሜጋ መደብር ያገኘናቸው አቶ ለማ አሸናፊ መጻሕፍቱን ኢትዮጵያውያንም የሚገዙ ቢሆንም በብዛት የሚገዙት ግን የውጭ አገር ሰዎች መሆናቸውን ገልጸውልናል፡፡ የእነዚህ መጻሕፍት ከጊዜ ወደ ጊዜ በብዛት መታተም በውጭ አገር ዜጎች በኩል ያለውን አማርኛ ቋንቋ የመማር ፍላጎት ከፍ ማለት እንደሚያሳይም አቶ ለማ ያመለክታሉ፡፡ 
በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በፖለቲካዊና በባህላዊ ዘርፎች ለሥራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቆዩ የውጭ አገር ዜጎች በርካታ እየሆኑ ባሉበት፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሮ እየከፈቱ ባሉበት ሁኔታ አማርኛ ቋንቋን የማወቅና መሠረታዊ መግባቢያዎችን የማጥናት ፍላጎት እየጨመረ መምጣት የሚያስገርም አይሆንም፡፡ የውጭ አገር ዜጎቹ በሚሠሩበት ተቋም አማርኛ ምንም እንኳ የሥራ ቋንቋ ላይሆን ቢችል የሚኖራቸውን ቆይታ ቀለል ለማድረግ ከሰዎች ጋር ያላቸውን የግንኙነት አድማስ ለማስፋትም ቋንቋውን በተወሰነ መልኩ እንደሚያውቁ መገመት የበለጠ ምክንያታዊ ይሆናል፡፡ አማርኛ ብቻም ሳይሆን ኦሮምኛ፣ ትግርኛና ጉራጊኛ ያሉ ሌሎች ቋንቋዎችን እንኳ መስማት የሚችሉ የውጭ አገር ዜጎች እያጋጠሙ ነው፡፡ 
የውጭ አገር ዜጎች ፈረንጅ፣ ጃፓን፣ ቻይና ሌላም አማርኛ አይችሉም ብሎ በመደምደም ሰዎቹ እዚያው ባሉበት ያልተገባ ነገር መናገር መልካም አለመሆኑን፤ ነገሩ ኢትዮጵያዊ እንግዳ ተቀባይ፣ እንግዳ አክባሪ ነው ከሚለው ነገር ጋርም እንደሚጋጭ አስተያየት የሚሰጡ አሉ፡፡ በሌላ በኩል የውጭ አገር ዜጎች ኢትዮጵያ ውስጥ ሲኖሩ ከቋንቋ ጋር በተያያዘ ሊያጋጥማቸው የሚችል የተለያየ ችግር ቢኖርም በተለይም ፈረንጆች ነጭ በመሆናቸው ብቻ ባልተገባ መልኩ በተለያየ አጋጣሚ ቅድሚያና ልዩ ቦታ ማግኘታቸው ሌላው ገጽታ በመሆኑ ከግንዛቤ ሊገባ እንደሚገባ የሚናገሩም አሉ፡፡
source Ethioreporter

No comments:

Post a Comment