የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለማላዊና ለአስካይ አየር መንገዶች ኃላፊዎች ሾመ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የማላዊና አስካይ አየር መንገዶችን የሚያስተዳድሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎችን ሾመ፡፡
ከኢትዮጵያ
አየር መንገድ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፣ የአየር መንገዱ ዋና የፋይናንስ ኦፊሰር አቶ ቃሲም ገረሱ በቅርቡ
እንደ አዲስ ኩባንያ የተቋቋመውን የማላዊ አየር መንገድን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት እንዲመሩ ተሹመዋል፡፡ አቶ ቃሲም
በኢትዮጵያ አየር መንገድ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባልነትና በከፍተኛ የፋይናንስ ባለሙያነት የረዥም ጊዜ ልምድ ያካበቱ
ኃላፊ ናቸው፡፡
የማላዊ
ብሔራዊ አየር መንገድ ‹‹ኤር ማላዊ›› በኪሳራ ከተዘጋ በኋላ የማላዊ መንግሥት አየር መንገዱን በማፍረስ ማላዊ
ኤርላይንስ ሊሚትድ የተሰኘ አዲስ ኩባንያ መሥርቷል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲስ በተቋቋመው ኩባንያ ላይ የ49
በመቶ የባለቤትነት ድርሻ ገዝቷል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 25 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግና አንድ
ቦይንግ 737 እና አንድ ቦምባርዲየር ‹‹ኪው›› 400 አውሮፕላኖችን ለማላዊ ኤርላይንስ ለማቅረብ ተስማምቷል፡፡
አየር መንገዱን የሚመራው ከኢትዮጵያ አየር መንገድና ከማላዊ ኤርላይንስ በተውጣጡ ባለሙያዎች እንደሆነ ከስምምነት
ላይ ተደርሷል፡፡
የማላዊ አየር መንገድ ፈርሶ እንደ አዲስ የተቋቋመ ኩባንያ በመሆኑ፣ አቶ ቃሲም ከባድ ሥራ እንደሚጠብቃቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
በተያያዘም
በምዕራብ አፍሪካ የሚንቀሳቀሰው አስካይ አየር መንገድን እንዲመሩ አቶ ይስሃቅ ዘወልዲ ተመርጠዋል፡፡ አቶ ይስሃቅ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአሊያንስና የኮርፖሬት ስትራቴጂ ፕላኒንግ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ አቶ ይስሃቅ
በተለያዩ ኃላፊነቶች አየር መንገዱን ለረዥም ዓመታት ያገለገሉ ከፍተኛ የማኔጅመንት አባል ናቸው፡፡
የአስካይ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ለሦስት ዓመታት ያገለገሉት አቶ ቡሴራ አወል በአቶ ይስሃቅ የተተኩ ሲሆን፣ አቶ ቡሴራ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቺፍ ኮሜርሺያል ኦፊሰር ሆነው ተሹመዋል፡፡
አስካይ አየር መንገድ እ.ኤ.አ. በ2008 መመሥረቱ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ45 በመቶ የባለቤትነት ድርሻ አለው፡፡ አየር መንገዱ ሥራውን የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2010 ነው፡፡
መቀመጫውን
በሎሜ ቶጎ ያደረገው አስካይ በምዕራብና በመካከለኛው አፍሪካ 22 መዳረሻዎች ሲኖሩት፣ ሰባት አውሮፕላኖች አሉት፡፡
እንደማንኛውም ጀማሪ አየር መንገድ አትራፊ ያልነበረው አስካይ በአሁኑ ወቅት ትርፋማ መሆን እንደጀመረ ለጉዳዩ
ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ለዚህም የአቶ ቡሴራ ማኔጅመንት ቡድን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገ
ምንጮች አስረድተዋል፡፡
No comments:
Post a Comment