Sunday, February 17, 2013


ዕጩ ፓትርያርኮችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ኮሚቴው አስታወቀ


በየካቲት ውስጥ ለሚካሄደው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ምርጫ ዕጩዎች እንዲሆኑ በካህናትና ምዕመናን ሲሰጥ የነበረው ጥቆማ መጠናቀቁንና አስመራጭ ኮሚቴውም በምርጫ ሕጉ መሠረት ውይይት እያካሄደ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ያቋቋመው የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመንበረ ፓትርያርክ ባለፈው ዓርብ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ስድስተኛ ፓትርያርክ ይሆናል የሚሉትን በአካልና በፋክስ እንዲጠቁሙ በተላለፈው መሠረት በርካታ ካህናትና ምዕመናን ጥቆማቸውን ሲሰጡ ሰንብተዋል፡፡

ከካህናትና ከምዕመናን የተገኘው ጥቆማ ለአስመራጭ ኮሚቴው በግብዓት የሚያገለግል መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢው፣ ዕጩ ፓትርያርኮችን እስከ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ በሚያደርገው ውይይት ከለየ በኋላ የካቲት 16 ቀን ለሚካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባዔ እንደሚያቀርበው አስታውቀዋል፡፡

የጥቆማ አሰጣጡና የጸሎት ጊዜው በሰላም መጠናቀቁን የገለጸው አስመራጭ ኮሚቴው፣ በቀሪው ጊዜም በወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ፈጣሪያቸውን በጸሎት እንዲጠይቁ አሳስቧል፡፡

የካቲት 21 ቀን 2005 ዓ.ም. ለሚደረገው ስድስተኛው ፓትርያርክ ምርጫ ዕጩ የሚሆኑ አምስት ሊቃነ ጳጳሳት የካቲት 18 ቀን እንደሚታወቁ፣ ከምርጫውም በኋላ በዓለ ሲመቱ የካቲት 24 ቀን በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

No comments:

Post a Comment