Sunday, February 17, 2013


የኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ለሁለት የሚከፍለው የሕግ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ



-    ማኔጅመንቱ ለህንድ ኩባንያ እንዲሰጥ ተወሰነ
-    የዓለም ባንክ አቋሙን ከዋሽንግተን እንደሚያሳውቅ ገለጸ

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽንን ለሁለት ከፍሎ ራሳቸውን የቻሉ ሁለት ኮርፖሬሽኖችን ማቋቋም የሚያስችል የሕግ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀረበ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በረቂቅ አዋጆቹ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ ቀን ባይቆርጥም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኮርፖሬሽን በሚል የሚቋቋሙት ሁለቱ ተቋማት፣ ከሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ በይፋ ሥራቸውን እንደሚጀምሩ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በሚል ስያሜ የሚቋቋመው ተቋም የግድቦች ግንባታና የኃይል ማመንጨት ሥራ ላይ የሚሰማራ ሲሆን፣ ራሱን የቻለ ማኔጅመንት ይኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኮርፖሬሽን በሚል ስያሜ የሚቋቋመውን መሥሪያ ቤት እንዲያስተዳድር ደግሞ የህንዱ ኩባንያ ተመርጧል፡፡ የህንድ ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን የተባለው ኩባንያ 16 ሚሊዮን ዶላር ተከፍሎት የኃይል ማስተላለፊያ ኮርፖሬሽኑን ለሁለት ዓመት ያስተዳድራል፡፡ ምንጮች እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሥራ አመራር ቦርድ ለህንዱ ኩባንያ ሥራው እንዲሰጠው ወስኗል፡፡

በዚህ ውሳኔ መሠረት ከሐምሌ 1 ቀን 2005 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራውን ተረክቦ የኃይል ማስተላለፊያ ኮርፖሬሽኑን እንደሚያስተዳድር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ኤሌክትሪክ የማመንጨት ችግር እንደሌለበት በርካታ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ የኮርፖሬሽኑ ትልቅ ችግር ያመነጨውን ኃይል በብቃት ያለማዳረስ ነው ተብሎም ይገለጻል፡፡

ለህንዱ ኩባንያ ይህ ሥራ ሲሰጠው ኤሌክትሪክ ኃይል የማሰራጨት አቅም ያጎለብታል ተብሎ ነው ሲሉ ምንጮች ይገልጻሉ፡፡ የህንዱ ኩባንያ የሚቋቋመውን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ ኮርፖሬሽንን ለሁለት ዓመት እንዲያስተዳድረው በመወሰኑ፣ በዓለም አቀፍ የስቶክ ገበያ እንደደራለት ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለሁለት እንዳኪፈል መወሰኑን በጥንቃቄ የሚመለከቱ አሉ፡፡

የዓለም ባንክ ይህንኑ ጥርጣሬውን ይዞ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለ ነው፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚገልጹት፣ የዓለም ባንክ የሥራ ኃላፊዎች ባለፈው ሐሙስ በዚህ ጉዳይ ላይ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር መልቲላተራል ዲፓርትመንት ኃላፊ ጋር መወያየታቸው ተሰምቷል፡፡ የዓለም ባንክና የሌሎች አበዳሪዎች ሥጋት የነበረው ከዚህ ቀደም የተሰጡና ወደፊት የሚሰጡ ብድሮችን በተመለከተ ማን ኃላፊነት ይወስዳል የሚል ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ብድሮችን በተመለከተ የሕግ ማዕቀፍ ተዘጋጅቶ ኮርፖሬሽኑ ሁለት ቦታ ስለሚከፈል አስተማማኝ ዋስትና ይኖራል እያለ ነው፡፡ 

‹‹ብድሩን የሚከፍለው አንድ ተቋም ብቻ መሆን አለበት፤›› ሲሉ የዓለም ባንክ ኃላፊዎች በውይይቱ ወቅት መናገራቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን በውይይቱ ወቅት የዓለም ባንክ ቀጣዩን ውሳኔ አላሳወቀም፡፡ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ የዓለም ባንክ ለተለያዩ አገሮች ለኢነርጂ ሴክተር ከሚሰጠው የብድር ፖሊሲ በመነሳት ውሳኔውን ዋሽንግተን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ያሳውቃል፡፡ በውይይቱ ወቅት ይህን አቋሙን በግልጽ ማንፀባረቁ ታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ በአጠቃላይ ከምታገኛቸው ብድሮች ከ30 እስከ 40 በመቶ የሚሆኑት ለኢነርጂ ሴክተር የሚሰጡ ናቸው፡፡ 

No comments:

Post a Comment