የኢህአዴግና የሻዕቢያ ድርድር ተበጠሰ
ኳታር በተናጠል የጀመረችው ኢትዮጵያንና ኤርትራን የማሸማገል ሂደት መበጠሱ ተሰምቷል። ከሽምግልናው ዙሪያ የግብጽ ሚና ስለመኖሩ አመላካች ጉዳዮች አሉ እየተባለ ነው። በድርድሩ ኢህአዴግ በዋናነት እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው የትግራይ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደሚት/ ጉዳይ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።አቶ መለስ የኢትዮጵያን ወደብ እንደተራ ጉዳይ አሳልፈው በመስጠት ኤርትራን እንደ አገር እውቅና በሰጡበት ወቅት ድጋፍ ለማሰማት ቀዳሚ የነረችው ኳታር ከበረሃው ትግል ጀምሮ የሻዕቢያ ወዳጅ አገር እንደሆነች ይታወቃል።
ከዚሁ የከረመ ወዳጅነት በመነሳት ኳታር በ2008 ከኢህአዴግ ጋር ተፈጥሮ የነበረውን የጸብ ግድግዳ አፍርሳ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው በዋናነት ሁለቱን አገሮች መልሶ ለማስታረቅ በተያዘ እቅድ ስለመሆኑ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ። በተለይም አሁን ያለው የኤርትራ አስተዳደር እጣ ፈንታ አብዝቶ ያስጨነቃት ኳታር በኤርትራ ወደብ ሊዝ በማድረግ፣ ኢንቨስትመንት ላይ በመሳተፍና ልዩ ድጎማ በማድረግ ቀዳሚውን ስፍራ ስለምትይዝ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ላይ ታች ማለቷ እንደማይደንቅ ስምምነት አለ።
የጎልጉል ምንጭ የሆኑ ዲፕሎማት እንዳሉት ኳታር አሁን እርቁን የፈለገችው በኤርትራ መረጋጋት እንዲፈጠርና የኤርትራ ኢኮኖሚ አንዲያገግም ለማድረግ በሚል ነው። በሌላ በኩል ህወሃት የዘወትር ስጋቱ የሆነውን ሻዕቢያን ለማስወገድ ሌት ከቀን እንደሚሰራና ይህም በድርጅት ደረጃ አቋም የተያዘበት ጉዳይ በመሆኑ የኤርትራ መንግስት መሰረታዊ የአቋም ለውጥ ሳያደርግ ከኢህአዴግ ጋር የድርድር ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ሁሉም ወገኖች የሚረዱት ጉዳይ ነው።
ከውስጥም ከውጪም ፖለቲከኞች ትኩረት ሰጥተው እየተከታተሉት ያለው የሁለቱ አገሮች የሰላም ድርድር ዲፕሎማቱ እንዳሉት ሁለት አብይ ጉዳዮች አሉበት። ሁለቱ አብይ ጉዳዮች ደግሞ ሊነጣጠሉ አይችሉም። በኤርትራ እለት እለት እየሰለለ የሄደው የአገሪቱ ኢኮኖሚና የኑሮ ውድነቱ የኢሳያስን አስተዳደር አናግቶታል። በተጨማሪ ሆን ተብሎ ይሁን በሌላ ምክንያት ከሃያላኑ አገራት ጋር የገጠሙት የረዥም ጊዜ ፍትጊያ የኢሣያስን ትከሻ አዝሎታል። ከዚህም በላይ እድሜ ለመለስ የፍቅር ጊዜያቸው ሲሻግት “አሸባሪ” አድርገዋቸው።
ከዓለምና ከአህጉር መድረኮች ሙሉ በሙሉ ተገልሎ የከረመው የኢሳያስ አስተዳደር በተለያዩ ደረጃዎች የደረሰበትን እግድና ቅጣት ለመቋቋም የዲፕሎማሲ ዘመቻ የጀመረው ከውጪ ያለውን ችግር ተከትሎ በአገር ውስጥ የገጠመውን ፈተና ለመቋቋም እንደሆነ ተንታኞች ያስታውሳሉ። በውስጥ የፖለቲካና የኢኮኖሚ አጣብቂኝ ውስጥ ያለው ሻዕቢያ ወንበሩ እየወላለቀ ስለሆነ ከቀድሞው ወዳጁ ህወሓት ጋር ለመወዳጀት ይፈልጋል።
ኤርትራ ኢኮኖሚዋ እንዲነቃቃ ኢትዮጵያን የንግድ ሸሪኳ ማድረግ የመጀመሪያው ስራ ነው። ያለ ስራ “ሙት” ሆኖ የተቀመጠውን የአሰብን ወደብ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ባነሰ ዋጋ እንድትጠቀምበት ማድረግና ወደቡ ላይ ህይወት መዝራት ዛሬ ላይ ግድ እየሆነ የመጣ ጉዳይ ነው። በተለይም ኢትዮጵያ ጅቡቲ ላይ የራስዋን ወደብ ለመገንባት የጀመረችው እንቅስቃሴና ለጅቡቲ የወደብ ኪራይ የምትገፈግፈው እጅግ ከፍተኛ ወጪ ግማሹ እንኳን ኤርትራ ቋት ውስጥ ቢገባ አሁን የተፈጠረውን የኑሮ ግለት ጋብ እንደሚያደርገው በርካቶች ይስማሙበታል።
በዚሁ መነሻ የኢሳያስ መንግሰት ከገባበት የመኖርና አለመኖር ስጋት ለመገላገል እቅድ ተነድፎለት የተጀመረውን ድርድር ኢህአዴግ የህልውና ጥያቄ በመጠየቁ ሳቢያ ብዙም ሳይራመድ በእንጭጩ ተኮላሽቷል። ኢህአዴግ በድርድሩ መሰረታዊ ሃሳብም ሆነ በሌሎች ዝርዝር የኢኮኖሚ ነጥቦች የተፈለገው ርቀት ድረስ ለመጓዝ ፈቃደኝነቱን ለመግለጽ ጊዜ አልወሰደም ነበር። የለበጣም ቢመስልም አቶ ሃይለማርያም አስመራ ድረስ ለመሄድ ዝግጁ መሆኑንን ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
የሆነ ሆኖ ኢሳያስ አሁን ባላቸው የፖለቲካ አቋም ከሳቸው ጋር መነገድ የዛለውን ክንዳቸውን ማፈርጠም በመሆኑ ኢህአዴግ እንዳልተዋጠለት የሚጠቁሙት ዲፕሎማቱ “ፖለቲካዊ ይዘቱ ኢኮኖሚያዊ ሽርክናውን ዋጋ ቢስ አድርጎታል” በማለት ስለማይነጣጠሉት ሁለት ተያያዥ ጉዳዮች አስረድተዋል።
ኳታር ሶማሊያ ላይ በነበራት አቋምና የገንዘብ ተሳትፎ ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት የዲፕሎማሲ መስመር ከመቋረጡም በላይ “ለሶማሊያ ጉዳይ አባቱ ነኝ” ይሉ በነበሩት አቶ መለስ ክፉኛ ተዘልዝላ ነበር። ያ ሁሉ አልፎ ዛሬ በኢንቨስትመንት ስም እርቅ አውርዳ የገባቸው ኳታር በጀመረችው ድርድር ኢህአዴግ ያነሳው መሰረታዊ የህልውና ጥያቄ አላላውስ ብሏታል።
ተቀማጭነታቸው ሎንደን የሆነ የጎልጉል ምንጭ እንዳሉት የኢህአዴግ ለመደራደሪያ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው አጀንዳ ኤርትራ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የትግራይ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደሚት/ ታጣቂ ሃይሎች ተላልፈው እንዲሰጡት ወይም ወደ ትግራይ ድንበር እንዲገፉለት ነው።
ቀደም ሲል የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ህወሃት አካል የነበሩት እነዚህ ክፍሎች “ኤርትራ ውስጥ ታግተው የተቀመጡ” ሃይሎች ስለመሆናቸውና ከ30 እስከ 40 ሺህ የሚደርስ ወታደር እንዳላቸው ለህወሃት ቅርበት ባላቸው የተለያዩ መገናኛዎች መዘገቡ ይታወሳል። በገለልተኛነታቸው የሚታወቁ መገኛዎችም ቢሆኑ የደሚት ሃይል ከአርበኞች፣ ከቤንሻንጉል፣ ከጋምቤላ፣ ከአማራ፣ ወዘተ ብረት አንጋቢዎች ጋር በጥምረት ለመሥራት መዘጋጀቱንና ይህም ሁኔታ ለህወሃት ስጋት እንደሚሆን አመልከተው ነበር።
ከኢህአዴግ የሚወጡ የምርመራ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ህወሃት ደሚትን እየፈራ ነው። ደሚት “በኤርትራ የታገተ ሃይል ነው” በማለት የድርጅቱን ሃይል ለማጣጣል ቢሞከርም፣ የደሚት ሃይል እንደሚባለው አለመሆኑንን የሚያረጋግጡ መረጃዎች አቶ መለስ በህይወት እያሉ ቀርቦላቸዋል። ከዚያ በኋላ ነበር ደሚት ጥንካሬው እንዳይጎለብት ህወሃቶች መስራት የጀመሩት።
በወቅቱ ከኢህአዴግ ጓዳ ያፈተለኩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ አሰብን ለመጠቀም የሚያስችላት ድርድር ተጀምሮ ነበር። በስዊድን የሚኖሩ የጎልጉል ምንጭ የሆኑ የኤርትራ ተወላጅ ከዓመት ከስድስት ወር በፊት የአሰብ ወደብ እንዲታደስና ስራ እንዲጀምር ተወስኖ እንደነበርና ስራው ሲጀመር ስራ አቁመው የነበሩ ሰራተኞችና አገልግሎት አቋርጠው የነበሩ ድርጅቶች ስራቸውን እንዲጀምሩ መመሪያ ተሰጥቶ እንደነበር ያስታውሳሉ። ስራው አሁን በምን ደረጃ እንደሚገኝ ለጊዜው መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
በተለያየ ወቅት አቶ መለስን ከቀድሞው ወዳጃቸው አቶ ኢሳያስ ጋር መልሶ ለማሻረክ ግብጽን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች እንደተሳተፉ የሚገልጹ አሉ። የግብጽን የሸምጋይነት ሚና ጥርጥር ውስጥ በማስገባት አስተያየት የሚሰጡት ዲፕሎማት አሁን ኳታር ከጀመረችው ድርድር ጋርም ግብጽን ያያይዛሉ። ከኳታር ካዝና በሚወጣ ገንዘብ ሻዕቢያ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች እንዲያደራጅ አጥብቃ የምትሰራውና የምትደጉመው ግብጽ አሁንም ቢሆን ኢትዮጵያና ኤርትራ አስተማማኝ ሰላም አውርደው በሰላም በጉርብትና እንዲኖሩ አትመኝም።
ኳታር ግን በቀድሞው አቋም መቀጠሉ አግባብ እንዳልሆነና በ2008 ከኢትዮጵያ ላይ እጇን እንድታነሳ ተጠይቃ ባለመቀበሏ የተሰበረው የዲፕሎማሲ ግንኙነት ለማቃናት መስራት የጀመረችው ከሊቢያው መሪ ጋዳፊ ሞት በኋላ እንደሆነ የሚገልጹ ክፍሎች ኳታር አሁን በጀመረችው “የትልቅ አገር ነኝ” ስሜትና በአፍሪካ ቀንድ ጂኦ ፖለቲካ ላይ ያላት ሚና መጎልበት ኢትዮጵያን መወዳጀት ብቸኛው አማራጯ እንደሆነ ይናገራሉ።
ሻዕቢያ እየከሰመ ሲሄድ ኢህአዴግ በሌላ በኩል በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ማደጉ ለንግድና ለፖለቲካ ዝናዋ ኢህአዴግን መወዳጀት አማራጭ የሌለው ጉዳይ የሆነባት ኳታር ሩጫዋ በጊዜ የተኮላሸው ከኢህአዴግ ወገን በተነሳ “የማይታሰብ” በተባለ ጥያቄ ነው። የደሚት የጦር ሃይል ተላልፎ እንዲሰጠው ወይም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር እንዲገፋለት የተየቀው ኢህአዴግ ይህ እስካልሆነ ድረስ ከሻዕቢያ ጋር አንድ መቀመጫ ላይ ተቀምጦ ለመነጋገር አለመቻሉ ለኳታር ሽምግልና የመጀመሪያውና ሊመለስ ያልቻለ ፈተና ሆኗል።
ከድሮ ጀምሮ አድብታ የኢትዮጵያን ተቃዋሚዎች በመርዳት የምትታወቀው ግብጽ ኢህአዴግ በፈለገው መልኩ ድርድሩ ሊካሄድ እንደማይችል አቋም ይዛ እየሰራች እንደሆነ፣ ለዚህም ሲባል ከአንዳንድ የተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ለመነጋገርና በሻዕቢያ አማካይነት ድጋፍ ለመስጠት ፍላጎት ማሳየቷን የጎልጉል ምንጭ የሆኑት ዲፕሎማት አስረድተዋል። ዲፕሎማቱ በደፈናው ከመናገር ውጪ ግብጽን ያነጋገረቻቸውን የተቃዋሚ ሃይሎች አልዘረዘሩም።
ኳታር የምጽዋን ወደብ በሊዝ ከመያዟ በተጨማሪ ለአሰብ ወደብ የነዳጅ ማጣሪያ ማደሻና ለወደቡ ስራ ማስቀጠያ ድጋፍ ማድረጓ አይዘነጋም። ያለ ስራ ተቀምጦ የነበረው ወደብ ለስራ እንዲዘጋጅ የታሰበው ለማን ተብሎና ማን እንዲጠቀምበት ታስቦ ነው ሚለው ጉዳይ ፖለቲካዊ ውሳኔ የሚጠይቅ አብይ ጉዳይ ከሆነ ዓመት ከስድስት ወር አስቆጥሯል። ኢህአዴግ የሚደጉመው የኤርትራ የሽግግር መንግስት አዲስ አበባ መቋቃሙም የሚታወስ ነው።
No comments:
Post a Comment