Tuesday, April 23, 2013

“የህዳሴዉ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም 19.6 ደርሷል” ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ 

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የስምንት ወራት የመንግስት አፈፃፀም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ እንዳሉት መንግስት የገንዘብ ዝውውርን ለመቆጣጠር የፍጆታ ሸቀጦች በማቅረቡ የዋጋ ንረት መጠን ከሁለት አሃዝ ወደ 7 ነጥብ 6 ወርዷል፡፡ በዚህ ረገድ የታየውን ውጤት ለማስቀጠልም ይሰራል ብለዋል፡፡“የህዳሴዉ ግድብ ግንባታ አፈፃፀም 19.6 ደርሷል” ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ
ኢትዮጵያ በ2004 ዓ.ም 8 ነጥብ 5 በመቶ የኢኮኖሚ እድገት እንዳስመዘገበች የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በዚህም ግብርናው 4 ነጥብ 9 ከመቶ፣ ኢንዱስትሪ 13 ነጥብ 6 በመቶ፣ አገልግሎት 11 ነጥብ 1 በመቶ ድርሻ አላቸው ነው ያሉት፡፡ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው እድገት ከሌሎች ሀገራት ጋር ሲነፃፀርና የሚሊኒየሙን የልማት ግብ ለማሳካት ከሚያስፈልገው እድገት አንፃር ሲታይ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ከእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አንፃር ሲታይ ግን እድገቱ የቀነሰ በመሆኑ በቀጣይ ሁለት ዓመታት ለማካካስ እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አረጋግጠዋል፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የ10 ነጥብ 5 አማካኝ እድገት መመዝገቡን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን እድገት ለማስቀጠል መንግስት የማስፈፀም አቅሙን ለማሳደግና ግልፅኝነትና ተጠያቂነትን ለማስፈን ትኩረት ይሰጣል፣ የአገር ውስጥ የገንዘብ አቅምንና የህዝብ ተሳትፎን ለማሳደግ እንዲሁም ዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ግብዓት ለማቅረብ ትኩረት ይሰጣል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ከወጪ ንግድ 2 ቢሊዮን ዶላር ተገኝቷል፡፡ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 6 ነጥብ 4 እድገት እንዳሳየ ገልፀዋል፡፡ ከአገር ውስጥ ገቢም ከ70 ቢሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል ብለዋል፡፡
ፈጣንና ዘላቂ ኢኮኖሚ ለማረጋገጥና የህብረተሰብ ኑሮን ለማሻሻል መንግስት ለትምህርትና ለጤና ዘርፍ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚህም የአንደኛ ደረጃ የትምህርት ሽፋን 94 በመቶ እንደደረሰና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ለማስፋፋትና ጥራቱን ለማስጠበቅ ይሰራል ብለዋል፡፡
መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተማሪዎች የቅበላ አቅም 320ሺ እንደደረሰ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መንግስት ለሳይንስ ፈጠራ ሰጠው ትኩረት ወደ ተቋማቱ ከገቡት ተማሪዎች 75 በመቶ ለተፈጥሮ ሳይንስ 25  በመቶ ደግሞ በማህበራዊ ሳይንስ እየተሰማሩ ነው ብለዋል፡፡
በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መጨረሻ 10 ሺ ሜጋ ዋት ኃይል ለማመንጨት በተያዘው ግብ መሰረት እየተገደቡ ካሉት ግድቦች ውስጥ ግዙፍ የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እስከአሁን 19 ነጥብ 6 በመቶ ተጠናቋል፣ በዚህ ዓመት መጨረሻም ወደ 26 በመቶ ግንባታው ለማገባደድ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡ የግልገል ግቤ3 አጠቃላይ የፕሮጀክት አፈፃፀምም 71 በመቶ መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገልፀዋል፡፡
የገጠር መንገድ ተደራሽነትን ለማስፋት የተያዘው እቅድም በአግባቡ እየተተገበረ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገልፀዋል፡፡ የአዲስ አበባ የቀላል ባቡር መስመር ግንባታም 26 በመቶ በእቅዱ ተፈፅሟል ነው ያሉት፡፡
በጤናው ዘርፍ የጤና አገልግሎት ሽፋንን ለማሳደግ ሰፊ ስራ የተከናወነ ቢሆንም በጥራት ማረጋገጥ ረገድ ግን የሚቀር ነገር አለ፣ ለዚህም ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡
የተፋሰስ ስራችን በሁሉም ክልሎች በሚባል ደረጃ በጥራት ተሰርቶ ዉጤት ተገኝቷል፣ በዚህም ሀገሪቱ በአረንጓዴ ልማት አርዓያነቷን አሳይታለች ብለዋል፡፡
በክልሎች ለዘመናዊ ትላልቅ እርሻዎች ሊሆኑ የሚችሉ መሬቶችን ከክልሎች ጋር በመነጋገር ተለይተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጣዩ ስራ ይህን የሚያለሙ ባለሃብቶችን ወደ ስፍራዎቹ ማስገባት ይሆናል ብለዋል፡፡
የአገር ውስጥ የቁጠባ ባህል ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች በ2002 የነበረው የ5 በመቶ አፈፃፀም ወደ 16 ነጥብ 5 በመቶ እንደደረሰ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዚህ ውጤት ላይ ተመርኩዞ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱን ለማሳካት ይሰራል ብለዋል፡፡
በወጪ ንግድ በኩል በተለይ ለጨርቃ ጨርቅና ለቆዳ ኢንዱስትሪዉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነዉ ያሉት አቶ ኃይለማርያም ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን የማደራጀትና የማስፋት ስራም መከናወኑን ተናግረዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች የኢንዱስትሪው ዋና አንቀሳቃሽ መሆን ደረጃ ላይ አልደረሱም፣ የውጭ ባለሃብቶች ያላቸዉ ተሳትፎም  በቂ አይደለም፣ ስለሆነም  የቀጣይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዋና አንቀሳቃሽ ለሚሆነዉ ኢንዱስትሪው ባለሀብቶች ድጋፍ ለማድረግ በስፋት ይሰራል ብለዋል፡፡

የንግድ ኢንተርፕራይዝ በማቋቋም የፋብሪካ ምርቶች ቅናሽ ካለባቸው ሀገራት ሸቀጦችን በመግዛት የፋብሪካ ምርቶች ዋጋ ጭማሪን ለማረጋጋት መንግስት አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ የተረጋጋና ጤናማ የኢኮኖሚ እድገት ለመፍጠር የተሰሩ ስራዎች አመርቂ እንደነበሩና ይህንን ለማስቀጠልም መንግስት እንደሚሰራ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ባቀረቡት ሪፖርት አረጋግጠዋል ፡፡
ህገወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታትና የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣን ለማድረግ የተጀመረውን ጥረት በይበልጥ ለማስቀጠል እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ በ2005 ተካሄደው የአካባቢ፣ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደር ምክርቤቶች ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊና የህዝብን ተአማኒነት ያገኘ ምርጫ ሆኖ እንደተጠናቀቀም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር በመብራት፣ መንገድ፣ ባቡርና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ለመተሳሰር እየሰራች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከኤርትራ በስተቀር ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ጋር የጋራ የልማትና የድንበር ኮሚሽን አቋቁመን እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
ከሁሉም ጎረቤት ሀገራት ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ሚናዋን እየተጫወተች ነው ብለዋል፡፡ በሱዳንና በደቡብ ሱዳን መካከል ስምምነት እንዲፈረምና እንዲተገበር ሀገራችን ከሌሎች አጋር አካሎች ጋር በመሆን ሰርታለች፣ በዚህም ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንዳሉት ዋና ጠላታችን ድህነትና ኃላቀርነት በመሆኑ ይህን  ለማስወገድ የምናደርገዉን ጥረት ለማስተጓጎል የሚሞክር ኃይልን አምርረን እንታገለዋለን፡፡ በኃይማኖት ሽፋን የሚደረግ እንቅስቃሴ የሽብር ኃይሎች አጀንዳ ማስፈፀሚያና ፀረ ህገ መንግስት በመሆኑ ግልፅና የፀና አቋም በመያዝ አምርረን እንታገላለን ብለዋል አቶ ኃይለማርያም፡፡ መከላከያ ሰራዊቱም ሽብርተኝነትንም ሆነ ማንኛውንም አፍራሽ ተግባር መመከት በሚያስችል መልኩ ሲገነባ ቆይቷል፣ አሁንም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በግንቦት ወር የሚካሄደውን የአፍሪካ ህብረት 50ኛ ዓመት የወርቅ ኢዮበልዮ በዓል በድምቀት ለማክበር ኢትዮጵያ ሚናዋን እየተወጣች ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በተለይም ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር በመሆኗ በአፍሪካ ሀገራት የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት እንደዚሁም በዓለቀፍ መድረኮች የአፍሪካ አቋም ለማንፀባረቅ እየሰራች ነው ብለዋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment