Monday, January 7, 2013


from:ethiopianreporter.com

ባለሀብቶች ቃል የገቡትን ገንዘብ ባለመስጠታቸው የኢሕአዴግ ፕሮጀክት ተስተጓጎለ

ባለሀብቶች ለኢሕአዴግ ዋና መሥርያ ቤት ሕንፃ ግንባታና ለካድሬዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ግንባታ እንሰጣለን ያሉትን ገንዘብ ሙሉ በመሉ ባለመስጠታቸው የዋና መሥርያ ቤት ሕንፃ ግንባታው መስተጓጐሉን የድርጅቱ አንድ ባለሥልጣን ገለጹ፡፡
አራት ኪሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አካባቢ ይገነባል የተባለው የኢሕአዴግ ፖለቲካ የሚቀመርበት ዋና መሥርያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ቢስተጓጎልም፣ እስካሁን ድረስ በተገኘው ገንዘብ ከአዲስ አበባ ወደ ባህር ዳር በሚወስደው መንገድ ላይ በኦሮሚያ ክልል ሱሉልታ ከተማ የካድሬዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት እየተገነባ ይገኛል፡፡

በመጪው መጋቢት በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የኢሕአዴግ ዘጠነኛው ጉባዔ ላይ በእነዚህ ጉዳዮች ዙርያ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የኢሕአዴግ ጉባዔ ላለፉት ዓመታት በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የፓርቲው ሕገ ደንብ እስከ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ዕድል ይሰጣል፡፡ በመሆኑም ጉባዔው በመጋቢት ወር ይካሄዳል ተብሏል፡፡ ከድርጅቱ  የተገኘነው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በኢሕአዴግ ደረጃ የአምስት ዓመት ዕቅድ በመታቀዱና አገሪቱም ይህንኑ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እየተገበረች በመሆኑ፣ በዕቅድ ዘመኑ አጋማሽ ላይ ጉባዔው እንዲካሄድ ተወስኗል፡፡ 

ከአራት ዓመት በፊት ኢሕአዴግ ሰባት ፎቅ ከፍታ ያለው ሕንፃና ከአዲስ አበባ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ሰንዳፋ ከተማ የካድሬዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ለመገንባት ዕቅድ ይዞ ነበር፡፡

በወቅቱ እነዚህ ግንባታዎች 130 ሚሊዮን ብር እንደሚፈልጉ ተገልጿል፡፡ የእነዚህን ግንባታዎች ዲዛይን የሠሩት ኤምኤች ኢንጂነሪንግና አልቲሜት ፕላን ኩባንያዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ዲዛይኖቹን ለኢሕአዴግ ያስረከቡት በነፃ ነው፡፡ የኢሕአዴግን የግንባታ ዕቅድ የተረዱት የአገሪቱ ታላላቅ ባለሀብቶች ወዲያው ነበር ፕሮጀክቱን ፋይናንስ ለማድረግ የተንቀሳቀሱት፡፡

ባለሀብቶቹ በሚሠሩት የሥራ ዘርፍ እየተፈላለጉ ለምሳሌ በአስመጪና ላኪ ዘርፍ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች እያንዳንዳቸው ከመቶ ሺሕ ብር እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ድረስ ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡ ነገር ግን ከአራት ዓመት በኋላ ከባለሀብቶቹ መካከል የተወሰኑት ቃል የገቡትን ገንዘብ ሙሉ በሙሉ አላስገቡም ሲሉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ሁለቱንም ግንባታዎች በአንድ ወቅት ለማስጀመር ዕቅድ ይዞ የነበረው ኢሕአዴግ፣ ሙሉ ለሙሉ ገንዘቡን ባለማግኘቱ ባገኘው ገንዘብ የካድሬዎች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ላይ ብቻ ትኩረት ለማድረግ መገደዱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ይህ ትምህርት ቤት ቀደም ሲል ሰንዳፋ በኬ ከተማ ይገነባል የሚለው ዕቅድ ተሰርዞ ነው በሱልሉታ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው፡፡

ትምህርት ቤቱ የተማሪዎችን ዶርም ጨምሮ የተለያዩ ግንባታዎችን አቅፎ የያዘ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ከስድስት ሚሊዮን በላይ አባላት ያሉት ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲው የሚፈልገውን አባል እየለመለመ ይህን ትምህርት ቤት በመጠቀም እየቀረፀ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

No comments:

Post a Comment