Monday, January 7, 2013



from:ethiopianreporter.com

ከረጲ ቆሻሻ 50 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ስምምነት ተፈረመ




 ከረጲ ቆሻሻ 50 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ስምምነት ተፈረመ




ባለፈው ዓርብ ምሽት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ለአዲስ አበባ ራስ ምታት ሆኖ ከቆየው የረጲ ቆሻሻ 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችለውን ስምምነት አድርጓል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ይህንን 50 ሜጋ ዋት የሚያመነጨውን ጣቢያ ለማስገንባት 120 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያደርጋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበና የኤሌክትሪክ ማመንጫውን የሚገነባው የእንግሊዝ ኩባንያ ካምብሪጅ ኢንዱስትሪ ሊትድ ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ሮበርት ሲአብሮክ ስምምነቱን ተፈራርመዋል፡፡

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል፣ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢኮኖሚ አማካሪ አቶ ነዋይ ገብረ አብ፣ የፌዴራል አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ተወልደ ገብረ እግዚአብሔር ተገኝተዋል፡፡

በወቅቱ ንግግር ያደረጉት ዶ/ር ተወልደ ይኼንን ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ከካርቦን ልቀት ነፃ ለመሆን የያዘችውን ዕቅድ ለማሳካት የጀመረቻቸው ሥራዎች አካል ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የረጲ ቆሻሻ ላለፉት አርባ ዓመታት ሲከማች የቆየና ለአዲስ አበባ አስተዳደር ራስ ምታት የሆነ ቦታ ነው፡፡

ክምችቱ ከአራት ፎቅ በላይ ሆኖ ላለፉት 42 ዓመታት የተጠራቀመ በመሆኑ፣ ለከርሰ ምድር ውኃ ብክለት ከመሆኑም በላይ፣ ለአካባቢው መጥፎ ገጽታ ከመስጠት በተጨማሪ በጤና ላይ ጉዳት ሲያስከትል ቆይቷል፡፡

አስተዳደሩ ይህንን የቆሻሻ ቦታ የዘጋው ሲሆን በቀጣይነት ሰንዳፋ አካባቢ ዘመናዊ የቆሻሻ ማስወገጃ ለመገንባት ታቅዷል፡፡ ነገር ግን የረጲ ቆሻሻ መጣያ ከሦስት መቀባበያ ሥፍራዎች አንዱ ሆኖ መገኘቱን ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ ባካሄደው ጥናት ተመራጭ ሆኗል፡፡

የካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ የምሥራቅ አፍሪካ ማኔጀር አቶ ሳሙኤል ዓለማየሁ እንደገለጹት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫው የሚገነባው አዲስ በሚጣሉ ቆሻሻዎች ተመሥርቶ ነው፡፡

ከዚህ አካባቢ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ የኤሌክትሪክ መስመር ይገባል፡፡ አዲስ አበባ ከተማ ከምትጠቀመው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ15 በመቶ ያላነሰ ድርሻ ይኖረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ምክትል ዳይሬክተር አቶ አብዱል ሐኪም መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አማራጭ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን ማብዛት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ሌሎች አካባቢዎች ኤሌክትሪክ ቢጠፋ ከረጲ የሚመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል ላይጠፋ ይችላል ሲሉ አቶ አብዱል ሐኪም ገልጸዋል፡፡

  በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰፊ ልምድ ያለው የእንግሊዝ ኩባንያ የሆነው ካምብሪጅ ኢንዱስትሪስ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ጅማን ጨምሮ በሰባት ከተሞች ከቆሻሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚያስችለውን የአዋጭነት ጥናት አካሂዷል፡፡

ኩባንያው በሁሉም ከተሞች ባካሄደው ጥናት የሥራውን አዋጭነት የተረዳ መሆኑን፣ በቀጣይነት ወደ ሌሎቹ ከተሞች እንደሚገባ ታውቋል፡፡ ኩባንያው በአዲስ አበባ የተረከበው ጠቅላላ ሥራውን ነው፡፡

No comments:

Post a Comment