Sunday, February 17, 2013


ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንግሊዝ ጋር በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ተስማማሙ




ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእንግሊዝ ጋር በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር ተስማማሙ
    ሰሞኑን በኢትዮጵያ በጉብኝት ላይ የነበሩትን የእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኒክ ክሌግ ተቀብለው ያነጋገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ በሰብዓዊ መብትና በዴሞክራሲ ጉዳዮች ላይ ዙርያ ለመነጋገር የቀረበላቸውን ጥያቄ ተቀበሉ፡፡
ከእንግሊዝ ከፍተኛ ዕርዳታ ከሚያገኙት አገሮች በግንባር ቀደምትነት የምትጠቀሰው ኢትዮጵያ፣ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ላይ ለመነጋገርና የቀረበላትን ጥያቄ መቀበሏን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከለጋሽ አገሮች በተለይ ደግሞ ከእንግሊዝ ጋር ዲሞክራሲን ለማበልፀግና አብሮ ለመሥራት ፍላጎታቸው እንደሆነ መግለጻቸው ታውቋል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ ጀምሮ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ጉዳይ አሳሳቢ እንደሆነባት በመግለጽ የምትታወቀው እንግሊዝ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ትችት ስትሰነዝር ቆይታለች፡፡ አሁን አሁን ግን ኢትዮጵያን በመርዳት ከቀዳሚዎች መካከል እየሆነችው የመጣችው እንግሊዝ፣ በኢትዮጵያ ላይ ስታነሳው በቆየችው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ለመነጋገርና አብሮ ለመሥራት የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ይሁንታ ያገኘች ይመስላል፡፡ “በዲሞክራሲ ዕድገት በትክክለኛው ሒደት ላይ ብንሆንም የእንግሊዝና የሌሎች የበለፀጉ አገሮች ድጋፍ ያስፈልጋል፤” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡

ባለፈው ዓርብ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በጽሕፈት ቤታቸው ከእንግሊዝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኒክ ክሌግ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ ኢትዮጵያ የምትፈልገው ዕርዳታ ብቻ ሳይሆን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት እንዲጠናከር ነው ብለዋል፡፡ “ለተደረገልን ከፍተኛ ዕርዳታ እናመሰግናለን፡፡ ነገር ግን ከዕርዳታ ይልቅ ንግድ እንዲጠናከር እንፈልጋለን፤” ሲሉ ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡

በቅርቡ የቡድን ስምንት የበለፀጉ አገሮችን ሊቀመንበርነት የተረከበችው እንግሊዝ ስለሆነች፣ በአካባቢያዊና አኅጉራዊ የደኅንነትና የሰላም ጉዳዮችም ላይ በጋራ ለመሥራት ሁለቱም መሪዎች ተስማምተዋል፡፡ በንግድና በኢንቨስትመንት፣ በታክስ ጉዳዮች፣ በዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች፣ በግልጽነትና በመሳሰሉት ላይ በታክስ በጋራ ለመሥራት ማቀዳቸው ታውቋል፡፡ 

No comments:

Post a Comment