Monday, March 4, 2013

የነዳጅ መገኘት ዘገባዎችን ታሎው ኦይልና ማዕድን ሚኒስቴር አስተባበሉ 

በደቡብ ኦሞ የነዳጅ ፍለጋ ሥራ በማካሄድ ላይ የሚገኘው ታሎው ኦይል የተሰኘው የእንግሊዝ ኩባንያ 2.7 ቢሊዮን በርሜል የሚገመት የነዳጅ ክምችት አገኘ ተብሎ የተሰራጩ ዘገባዎችን ኩባንያውና የማዕድን ሚኒስቴር አስተባበሉ፡፡
ኢነርጂ ኤንድ ካፒታል የተሰኘው የአሜሪካ ድረ ገጽ ታሎው ኦይል 2.7 ቢሊዮን በርሜል ነዳጅ እንዳገኘ በዚህ ሳምንት የዘገበ ሲሆን፣ ዘገባውን የተለያዩ ድረ ገጾች ተቀባብለውታል፡፡ ታሎው ኦይል ኢትዮጵያ ባለፈው ዓርብ  በላከው መግለጫ ዘገባው ግራ የሚያጋባ ነው ብሏል፡፡

የታሎው ኦይል የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጴጥሮስ አበበ፣ የሳቢሳ አንድ ጉድጓድ (የመጀመርያው የነዳጅ ፍለጋ ጉድጓድ) ቁፋሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ታሎውም ሆነ አጋር ድርጅቶች ነዳጅ ስለመገኘቱ ያወጡት መረጃ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡ ‹‹የጉድጓድ ቁፋሮው ውጤት ከሁለት ወር በኋላ ይታወቃል ብለን የምንጠብቅ በመሆኑ፣ በዚያን ወቅት ውጤቱን በተመለከተ በድረ ገጻችን መግለጫ የምናወጣ ሲሆን፣ ለዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኅን እናሳውቃለን፡፡ ውጤቱ ታውቆና ተገምግሞ ሳያበቃ የምናወጣው መግለጫ አይኖርም፤›› ብለዋል አቶ ጴጥሮስ፡፡ የወጡትን ዘገባዎች በተመለከተም ሁልጊዜም ቢሆን የታሎው ኩባንያን መጠየቅ ወይም ድረ ገጹን መመልከት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡


የማዕድን ሚኒስትሯ ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ በበኩላቸው፣ ታሎው ኦይል በጋና፣ በኡጋንዳና በኬንያ ካከናወናቸው ስኬታማ ሥራዎች በመነሳት በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ከነዳጅ ፍለጋው ጋር በተያያዘ የተዛቡ ዘገባዎች እየወጡ ነው ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ስንቅነሽ እንደሚሉት፣ ታሎው በዘርፉ የቴክኒክ ብቃቱ የዳበረና በጥሩ ሁኔታ ሥራውን የሚያከናውን ድርጅት ነው፡፡ ኩባንያው በደቡብ ኦሞ ሦስት የፍለጋ ጉድጓዶች እንደሚቆፍር ገልጸው፣ የመጀመርያው ጉድጓድ ቁፋሮ እ.ኤ.አ ጥር 13 ቀን 2005 ዓ.ም. በይፋ መጀመሩን አስታውሰዋል፡፡

የመጀመርያው ጉድጓድ ቁፋሮ 1,500 ሜትር አካባቢ የደረሰ ሲሆን፣ ቁፋሮው የሚጠናቀቀው 2,600 ሜትር ላይ ይሆናል፡፡ ኩባንያው ለእያንዳንዱ ጉድጓድ ቁፋሮ 50 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡ የመጀመርያው ጉድጓድ ቁፋሮ ባልተጠናቀቀበት ሁኔታ ምንም ማለት እንደማይቻል ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የቁፋሮውን ሥራ አብረን እያየን ለኅብረተሰቡ ይፋ የምናደርገው ጉዳይ ካለም እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ታሎው ቀደም ሲል 18,000 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የሴስሚክ ጥናት ማድረጉን አስታውሶ፣ በተሰበሰበው የሴስሚክ ዳታ ተንተርሶ የመጀመርያው የፍለጋ ጉድጓድ የሚቆፈርበትን ቦታ እንደመረጠ ተናግሯል፡፡ የቁፋሮውን ሥራ በኮንትራት የወሰደው ‹‹ኦጂኢሲ›› የተሰኘ የፖላንድ ኩባንያ ነው፡፡

አንድ ከፍተኛ የፔትሮሊየም ኤክስፐርት እንደገለጹት፣ ታሎው በኬንያ ነዳጅ ማግኘቱ በደቡብ ኦሞ ነዳጅ ይገኛል የሚለውን ተስፋ አንሮታል፡፡ ባለሙያው እንደሚሉት፣ የጉድጓድ ቁፋሮ ተጠናቆ የሙከራው ውጤት ካልታወቀ በቀር በተሰበሰቡ መረጃዎች ብቻ ተንተርሶ ነዳጅ አለ ወይም የለም ማለት አይቻልም፡፡

‹‹እስካሁን ባለው ቴክኖሎጂ ጉድጓድ ተቆፍሮ ሙከራ ካልተደረገ በስተቀር በሴስሚክ መረጃና በሳተላይት ፎቶግራፎች ተደግፎ ነዳጅ መኖሩን በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡ የግራቪቲና ሴስሚክ ጥናቶች እንዲሁም ከሳተላይት የሚነሱ ፎቶግራፎች ለነዳጅ ፍለጋ ሥራ ከፍተኛ እገዛ ቢያደርጉም፣ በእነዚህ መረጃዎች ብቻ ክምችት እንዳለና እንደሌለ ማረጋገጥ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የሴስሚክ ጥናቱን በኮንትራት ከታሎው ኦይል የወሰደው ቢጂፒ ጂኦ ሰርቪስስ የሰበሰበው መረጃ አበረታች መሆኑን ሪፖርተር ተገንዝቧል፡፡ የታሎው ባለሙያዎች ከመጀመርያው ጉድጓድ ቁፍሮ መልካም ውጤት እንደሚጠብቁ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ሳቢሳ አንድ  ከኦሞራቴ ከተማ 15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በተጨማሪ የሚቆፈሩት ሁለት ጉድጓዶች ደግሞ በጨው ባህር አካባቢ ይገኛሉ፡፡ ባለሙያዎች እንደሚሉት፣ ነዳጁ ቢገኝ እንኳ የክምችቱን መጠን በትክክል ለማወቅ የሚሠራው የክምችት ግምት ሥራ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመት ይፈጃል፡፡   

No comments:

Post a Comment